የከተሞች የምግብ ዋስትና መጓተት በገዢው ፓርቲና በአለም ባንክ መካከል አለመግባባትን ፈጠረ

ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ‹‹የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮግራም በከተማ ኗሪ የሆኑ ‹‹በሚቀጥሉት 10 አመታት ከአጠቃላይ ድህነት ወለል በታች ያሉ 90 በመቶ የሚሆኑ ስራ አጦችን እንዲሁም ለማህበራዊ ኑሮ ችግርና ጠንቅ የተጋለጡ ዜጎች ወደ ስራ እንዲሰማሩና 10 በመቶ የሚሆኑት የመስራት አቅም የሌላቸው የማህበራዊ ጠንቅ ሰለባዎች የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት እንዲያገኙ›› የሚል አላማ ይዞ በ2005 ዓ.ም መጀመሪያ ይፋ የሆነው ፕሮግራም፣ እቅዱ በአብዛኛው በአለም ባንክ እርዳታ እንደሚፈጸም ተገልጾ ባንኩ ለመጀመሪያው ዙር እርዳታ ከ3 ዓመታት በፊት ገንዘብ ለቆ የነበረ ቢሆንም፣ የስራውን እንቅስቃሴ ለመታዘብ የመጡት የባንኩ ባለስልጣናት ስራው ሳይጀመር በማግኘታቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ አገሪቱ 150 ሚሊዮን ዶላር የዓለም ባንክ ደግሞ 350 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመደብ በእቅዱ ላይ ሰፍሯል። ገዢው ፓርቲ በመገናኛ ብዙሃን መርሃግብሩ መጀመሩን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም፣ የአለም ባንክ የፕሮጀክቱ ቁጥጥር እና ግምገማ መሪ ቡድን በተግባር የተመለከተው ግን እስካሁን ከተባለው ተቃራኒ የሆነ ነው። የአለም ባንክ ገዢው ፓርቲ ለእርዳታ የተላከውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋሉን አረጋግጧል፡፡ በድርጊቱ ያዘነው ባንኩ ቀጣይ ዙር ክፍያ እንዳይለቀቅ አግዷል። እገዳው ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል በሚል የተደናገጠው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ትግበራ እጀምራለሁ በሚል እየተሯሯጠ ይገኛል።