የኦፌዴንና የኦህኮ አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ

የኢህአዴግ መንግሥት በአሸባሪነት ወንጀል ክስ መስርቶ በእስር ላይ ካዋላቸው ስድስት ወር የተጠጋቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲ እና የመድረክ የአመራር አባል የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረንስ (ኦህኮ) ፓርቲ እና የመድረክ የአመራ አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ እና ሌሎች ሰባት የኦሮሞ ተወላጆች ዛሬ ታህሳስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም  ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ

መሪዎቹ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ከህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ሁሉም ጥፋተኞች እንዳልሆኑ ገልጠዋል።

ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች የተለያዩ ማስረጃዎች ከእስረኞቹ ቤቶች ሲወሰዱ መታዘባቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጠዋል። ከዚህ ውጭ ይህ ነው የተባለ ማስረጃ በሁለቱ አመራሮች ላይ አልቀረበም።

ኢሳት ያነጋገራቸው የኦፍዴን ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ፣ ምንም እንኳ ለኢሳት ቃለምልልስ መስጠት በሽብርተኝነት የሚያስከስስ ሆኗል በማለት ቢናገሩም የተሰማቸውን ስሜት ከመናገር እና የመጣውን ከመቀበል ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

አቶ በቀለ እንዳሉት  ግለሰቦቹ እስከሁን ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሳይሰጡ መቆየታቸው ፍርድ እንደተነፈገ ያሳያል እስረኞቹን ለመጠየቅ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም ዋና ጸሀፊው ይናገራሉ፡

እሰረኞቹ አካላዊ ጉስቁልና እንደሚታይባቸው አቶ በቀለ ገልጠው፣  በአመራሮቹ መታሰር ቤተሰቦቻቸው እየተሰቀያዩ በመሆኑ ኢትዮጵያኖች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ተማጽነዋል።

በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነተት ወንጀል የተከሰሱት ዘጠኝ ሰዎች ቀደም ሲል የፖለቲካ እስረኛ በመሆናቸው የመንግስትን የሀሰት ክስ ከማስተባበል ይልቅ ከፍርድ ቤቱ ጋር ምንም ዓይነት ፍትህን የመከላከል እርምጃ ሳይወስዱ በዝምታ ለመታሰር ወስነው የነበር ሲሆን አሁን ፓርቲዎቻቸው ቢያንስ ለመጪው ትውልድ የሀሰት ክሱ ሪከርድ ለታሪክ እንዲቀር ጠበቃ እንዳቆሙላቸው አቶ በቀለ አክለዋል።

 ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙት እስረኞች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከኦነግ ወይም በአገር ውስጥ በሰለማዊ ትግል ከሚታገሉት ከኦፍዴንና ከኢህኮ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ናቸው።