የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር አንድ ከፍተኛ አመራር ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጡ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 24/2009) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር አንድ ከፍተኛ አመራር በሶማሊያ መንግስት አማካኝነት ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ታወቀ።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር እንዳስታወቀው ሶማሊያ ውስጥ ተይዘው ለህወሃት መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አብዱልከሪም ሼክ ሙሴ ናቸው።

ላለፉት ሶስት አመታት ነዋሪነታቸውን በሞቃዲሾ አድርገው የቆዩት አብዱከሪም ሼህ ሙሴ ባለፈው ሳምንት ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ችግር ወደ ሶማሊያ ማእከላዊ ግዛት ጋልሙዲግ መሔዳቸውንና በጋልካዩ ከተማ በአካባቢው የጸጥታ ሃይል መያዛቸውን የኦጋዴን ነጻነት ግንባር አስታውቋል።

በህመም ላይ የምትገኘውን የእህታቸውን ልጅ ወደ ሞቃዲሾ ውስደው ለማሳከም በሄዱበት በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሞቃዲሾ የተወሰዱት የኦብነግ ከፍተኛ አመራር አብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ለቀናት በሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ከቆዩ በኋላ ተላልፈው መሰጠታቸውን መረዳት ተችሏል።

የሶማሊያ መንግስት ቤተሰብ እንዳይጎበኛቸው ከከለከለና እንደሚፈቱ ተስፋ ከሰጠ በኋላ ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጉ ተመልክቷል።

መላ ቤተሰባቸው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ታጣቂዎች የተገደሉባቸውን አብዱልከሪም ሼህ ሙሴን አሳልፎ መስጠት የተባበሩት መንግስታትን የ1954 ድንጋጌ የሚጥስና የራሱን የሶማሊያ ህገ መንግስት የሚቃረን ድርጊት መሆኑን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር አስታውቋል።

የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማግኘት ሲል አብዱልከሪም ሼህ ሙሴን ለመስዋእትነት አቅርቧል ሲልም ከሷል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳታፊ መሆናቸውንና ሁለቱን በስጋ የሚያዛምዱት በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትልቅ ሚና ማጫወታቸውን ኦብነግ በመግለጫው ዘርዝሯል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሊ ካሂር እንዲሁም የጸጥታው መስሪያ ቤት ሃላፊዎች የፖለቲካና የሞራል ተጠያቂነትንና ዋጋ የሚያስከፍል ትልቅ ስህተት መስራታቸውን ግንባሩ አስታውቋል።

ግንባሩ አብዱልከሪም ሼህ ሙሴን ለሶማሌ ጠላት ሕወሃት አሳልፎ ተሰጥቷል በማለት ወቅሷል።
ሕወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላትና የአፍሪካ ቀንድ ያለመረጋጋት መንስኤ ነው ሲልም አክሏል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር በመጨረሻም ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ለአለም አቀፉ ቀይ መስቀል እንዲሁም ለሂዩማን ራይትስ ዎች ጥሪ አቅቧል።
ለሶማሊያ የፓርላማ አባላት እንዲሁም ለተራማጅ ሃይሎች ሁሉ ድርጊቱን እንዲያወግዙ መልእክቱን አስተላልፏል።

ኦብነግ በተወሰደው ርምጃ ተስፋ እንደማይቆርጥ ይልቁንም ለሕዝብ ነጻነት የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ከሕወሃት ጋር የተባበሩ ሁሉ እያበቃለት ካለው ስርጸት ጋር አብረው እንደሚከስሙ አስጠንቅቋል።