የእስራዔል መንግስት በሃገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደም እንዳይለግሱ ጥሎ የቆየውን እገዳ አነሳሁ አለ

ኢሳት (ኅዳር 30 ፥ 2009)

የእስራዔል መንግስት በሃገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደም እንዳይለግሱ ጥሎ የቆየውን እገዳ አነሳ።

የእስራዔል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሃገሪቱ ውጭ የተወለዱ ወይም የHIV/AIDS ስርጭት ባለባቸው ሃገራት ለአንድ አመት ያህል ቆይታ ያደረጉ ቤት-እስራዔላዊያን ደም እንዳይለግሱ ከ10 አመት በፊት እገዳ መጣሉ ይታወሳል።

ይሁንና የእስራዔል መንግስት ጥሎ የነበረው እገዳ በአግባቡ ለህዝብ ይፋ ባልተደረገበት ወቅት ማሪቭ (maiariv) የተሰኘ የሃገር ጋዜጣ ከኢትዮጵያውያን ይወሰድ የነበረ ደም ሲወገድ መቆየቱን ማጋለጡ ሃርቴዝ ጋዜጣ አርብ ዘግቧል።

የእስራዔሉ የደም ባንክ የሚቆጣጠረው ማገድ ዴቪድ አደም የተሰኘው ኩባኒያ የወሰደውን ይህንኑ ዕርምጃ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተከታታይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና በምዕራባውያን ሃገራት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረው ድርጊት ለ10 አመት ያህል መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን ጋዜጣው አውስቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔውን ያስተላለፈው የእስራዔሉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ በደቡብ ምስራቅ ኤዢያ እና የካሪቢያን ሃገራት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል።

ይሁንና ውሳኔው በደቡብ አፍሪካ ያላከተተ ሲሆን የእስራዔሉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወሰደው ዕርምጃ በሃገሪቱ ውጥረት አስነስቶ የከረመውን የዘረኝነት ችግር ያረግበዋል ተብሎ ተገምቷል።

ለአስር አመት ያህል ጊዜ ተጥሎ የቆየው እገዳ ቢነሳም ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከአንድ አመት በላይ ቆይታ ያደረጉ ቤተ እስራዔላዊያን ወደ እስራዔል በተመለሱ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥም ደም መለገስ እንዳማይችሉ የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ሚኒስትሩ የወሰደው ዕርምጃ በኢትዮጵያ ላይ ለአመታት የቆየን ስልታዊ መድሎ መፍትሄ እንዲያገኝ ያደረገ ዕርምጃ ነው ሲሉ የተቃዋሚ ፓርት አመራር የሆኑት ኢሳቅ ሀርዞግ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1980 እስከ 1996 ዓም በብሪታኒያ የኖሩ ትውልደ እስራዔላውያን በወቅቱ በብሪታኒያ ተከስቶ ከነበረ የእንስሳት በሽታ ምክንያት አሁንም ድረስ በእስራዔል ደም እንዳይለግሱ እገዳ ተጥሎባቸው ይገኛል።

ሰሞኑን አንድ ታዋቂ እስራዔላዊ የግርዛት ባለሙያ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች በኢትዮጵያውያንና በሱዳናዊያን ህጻናት ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ያደረጉት ድርጊት በኢትዮጵያውያንና እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል።