የእርዳታ ምግብ አቅርቦት እጥረትን ተከትሎ 700ሺ ሰዎች ድጋፍ ሳያገኙ መቅረታቸው ተገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 25 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ያጋጠመውን የእርዳታ ምግብ አቅርቦት እጥረትን ተከትሎ በግንቦት ወር እርዳታ ማግኘት የነበረባቸው 700 ሺ አካባቢ ሰዎች ያለምንም ድጋፍ መቅረታቸው ተገልጿል።

በዚሁ የምግብ እጥረት ዙሪያ መግለጫን ያወጣው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ወደ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በከፍተኛ የምግብ ችግር ውስጥ መሆናቸው አስታውቀዋል።

ይሁንና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለእርዳታ ጥሪው በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰብዓዊ ቀውስ ይጋለጣሉ ተብሎ ተሰግቷል።

በግንቦት ወር ምንም አይነት ድጋፍ ያላገኙ 700ሺ ተረጂዎች በሰኔ ወርም ተመሳሳይ ችግር እንደሚያጋጥማቸው የህጻናት መርጃ ድርጅቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ በሃገሪቱ ያለው የእርዳታ ምግብ ክምችት በሰኔ ወር ሊያልቅ ይችላል ሲል ከቀናት በፊት ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

ይህንኑ ሪፖርት ተከትሎ ተመሳሳይ ሪፖርትን አርብ ያወጣው ዩኒሴፍ ከሃምሌ ወር ጀምሮ በምግብ እጦር የሚቸገሩ ሰዎች ቁጥር ወደ አስከፊ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል በፅኑ አሳስቧል።

“በደቡባዊ ኢትዮጵያ ያለው የድርቅ ሁኔታ ከመጥፎ ወደ አስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው” ያሉት በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ ጆን ግራም፣ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ዝናብ ማግኘት የማይጠበቅ በመሆኑ ድርቁ የሚያደርሰው ጉዳት እጅጉኑ እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል አስታውቀዋል።

መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቢያቀርቡም ባለፈው አንድ አመት ሊገኝ የቻለው ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ በሰው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቅረፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።

5.1 ሚሊዮን የነበረው የአስቸኳይ ምግብ ተረጂዎች ቁጥር በቅርቡ ወደ 7.7 ሚሊዮን አካባቢ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ቁጥሩ ዳግም ያሻቅባል ተብሎ ይጠበቃል።

መንግስትና የዕርዳታ ድርጅቶች ይጨምራል ተብሎ የሚጠበቀው ቁጥር በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉም ታውቋል።