የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ተሰግቷል

መጋቢት ፳፪ (ሃይ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የእህል ዋጋ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። በአዲስ አበባ ጤፍ እስከ 1700 ብር በመሸጥ ላይ ነው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ጤፍ በኩንታል እስከ 1500 ብር እየተሸጠ ነው። የእህል ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን ስኳርና ዘይትም ከገበያ ጠፍተዋል። ችግሮቹ ተደራርበው ህብረተሰቡን እያስጨነቁ ባለበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ደርቅ እንደገና ይከሰታል የሚል ሪፖርት መውጣቱ ህብረተሰቡን ማስደንገጡን ነው ዘጋቢአችን የላከው ዘገባ የሚያመለክተው።

 በኢትዮጵያ የአለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ የሆኑት ጁዲዝ ሹለር የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት ተከስቷል። በዚህም የተነሳ በተለይ በሰሜን ምስራቅ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ለምግብ ፍጆታ የሚለው የስኳር ድንች ተከላ ተስተጓጉሏል። በአማራ አካባቢ ደግሞ የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 3 በመቶ ብቻ የሆነው ማሳ ነው የተሸፈነው። በኦሮሚያና በትግራይም መረጃዎች ተመሳሳይ ናቸው ። የበልግ ምርቶች በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከ አጠቃላዩ የግብርና ምርት ከ5 እስከ 30 በመቶ ሲሸፍኑ በደቡብ ደግሞ ከ30 እስከ 60 በመቶ ይሸፍናሉ” ብለዋል።

ባለሙያዎች በዚህ አመት በመጋቢትና ግንቦት የሚታየውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ረሀብ ይከሰታል በማለት እያስጠነቀቁ ነው። የኢትዮጵያ የሜትሮሎጂ ባለሙያዎችም ሁኔታው ይሻሻላል ብለው እንደማይገምቱ እየገለጡ ነው።

የበልግ ዝናብ መጥፋት ገበሬዎች ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዳያወጡ የሚያድረጋቸው በመሆኑ ሰሞኑን የሚታየው የእህል ዋጋ በሚቀጥሉት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል በማለት አንድ ነጋዴ ለዘጋቢያችን ገልጧል። ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱን የተናገሩት ነጋዴው ፣ ህብረተሰቡ ነጋዴው አውቆ ዋጋ የሚጨምር የመስለዋል፣ ችግሩ የሚከሰተው ምርቱ ከገበያ በመጥፋቱ ነው፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ግን ምርት አለ ችግሩን የፈጠሩት ነጋዴዎች ናቸው በማለት ሸማቹን ከነጋዴው ለማጣላት ሌት ተቀን ይቀሰቅሳሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የእህል ዋጋ ጭማሪ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳሰበው መምጣቱን ዘጋቢያችን ገልጧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide