የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ሠራተኞች በቻይናውያን አሠሪዎቻቸው ድብደባ ደረሰባቸው

ሰኔ ፲፱( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሀዋሳ የቻይናውያን ኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሠራተኞች በቻይናውያን አሰሪዎቻቸው የከፋ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው በተለይ ለኢሳት ገለጹ።
የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እንደገለጹት በአሰሪዎቻቸው የከፋ ድብደባ የተፈጸመባቸው ላለፉት ወራት ያልተከፈላቸውን ደመውዝ እንዲከፈላቸው በጋራ ጥያቄ በማቅረባቸው ነው።
“የሠራንበት የላባችን ዋጋ ሊከፈለን ይገባል። የሠራንበትን ደመወዝ ባለማግኘታችን ቤተሰቦቻችን ችግር ላይ ወድቀዋል” በማለት ላቀረቡት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም የሚሉት ሠራተኞቹ፤ ይልቁንም እያመጻችሁ ነው በሚል በአሠሪዎቹ ከባድ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው በሀዘን ገልጸዋል።
ሠራተኞቹ የደረሰባቸውን በደል ለመግለጽና ፍትህ ለማግኘት ወደ ሀዋሳ ታቦር ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ያመሩ ሲሆን፤ይሁንና ያለምንም ከልካይ በተለያዩ ጊዜያት ሲፈጽሙ ከቆዩት በደል በመነሳት ፍትህ እናገኛለን የሚል ተስፋቸው ተሟጧል።
“ጉልበታችንን በርካሽ ገዝተውም፣ በዚያው ዋጋ ለሠራነው ሥራም ደመወዛችንን ከልክለውን፣ ደመወዝ ይከፈለን የሚል ጥያቄ ስናነሳ እየተደበደብን እንገኛለን” ያሉት ሠራተኞቹ፤ የሚመለከተው አካል ፍትሕ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲፈልግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ቻይናውያን ድርጅቶች ሴቶችን አስገድዶ ከመድፈር ጀምሮ በተደጋጋሚ በሠራተኞቻቸው ላይ በሚፈጽሟቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክስ ቢቀርብባቸውም ፍትሀዊና ትክክለኛ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ስለማይወሰድባቸው ችግሩ እየከፋ እንጂ እየተሻሻለ ሊመጣ አለመቻሉ በስፋት ይነገራል።