የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ የኦሮሚያ ቴሌቪዥንን ከሰሰ

ግንቦት ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክሱ ምክንያት ኤጄንሲው ከኦሮሚያ ክልል ወስዶት የነበረውን 200 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት አስመልክቶ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን በቅርቡ ያስተላለፈው ፕሮግራም ነው።
ኢንሳ በቀን 09-09-2009 ለአቶ ለማ መገርሳ በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ በ2002 ዓመተ ምህረት ለሥራ ኃላፊዎችና ለሠራተኞች መኖሪያ የሚሆን ካምፕ መሥሪያ መሬት የክልሉን መንግስት ጠይቆ በለገጣፎና በለገዳዲ መስተዳድር 200 ሺህ ሄክታር እንደተፈቀደለት በደብዳቤው አውስቷል።
200 ሺህ ካሬ ሜትር ማለት ርዝመቱ ከጃን ሜዳ ጋር የሚጠጋጋ ቦታ ማለት ነው።
ይሑንና መኖሪያ ካምፑን በመንግስት በጀት ለመሥራት የሚፈቅድ አሠራር ባለመኖሩ፤ የተፈቀደው መሬት ወደ ሠራተኞቹ እንዲዛወር ጥያቄ ማቅረቡንና ይህም በክልሉ መንግስት ተፈቅዶለት ወደ ሥራ መገባቱን ኢንሳ ገልጿል።
ከረዥም ዓመታት በኋላ በመሬቱ ላይ ወደ ሥራ መገባቱን ያወሳው ኢንሳ፤ሆኖም ሥራው በተጀመረ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ባላወቅነው ሁኔታ በቃል በተሰጠ ትዕዛዝ ሥራው እንዲቆም ተደርጎብናል ሲል ለክልሉ ፕሬዚዳንት በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።
ሥራው የቆመበት ምክንያት እንዲገለጽለት ለከተማ መስተዳድሩ በድብዳቤ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በማጣቱ ዳግም ለክልሉ ፕሬዚዳንት ደብዳቤ ጽፎ መልስ እየጠበቀ መሆኑን የጠቀሰው የደህንንት ኤጄንሲው፤ሁኔታው በዚህ ላይ እያለ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን በጉዳዩ ዙሪያ የሠራው ፕሮግራም ገጽታዬን ያበላሸ ነው ሲል ከሷል።
የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በኤጄንሲውና በክልሉ መንግስት መካከል የነበረውንና ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነት የሚያሻክርና የኤጄንሲውን ገጽታ በክልሉና በሀገሪቱ ህዝብ ዘንድ የሚያጠለሽ ነው ሲልም ኢንሳ ለአቶ ለማ መገርሳ ቅሬታ አቅርቧል።
ሚዛኑን ያልጠበቀና በርካታ የተፋለሰ መረጃ ያስተላለፈ ነው ያለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም የወቀሰው ኢንሳ፣የኤጄሲው አስተያዬት ሳይጣከልበት የተላለፈው ዘገባ ለጠላት ሚዲያ ግብአት ከመሆን በዘለለ እውነታውን ፈጽሞ የማይገልጽ በመሆኑ ኤጄንሲውንና የኤጄንሲውን ማህበረሰብ አሳዝኗቸዋል ብሏል።
ይሑንና ኢንሳ የጠላት ሚዲያ ያላቸው እነማንን እንደሆነ በዝርዝር አልጠቀሰም።
በመሆኑም የቀረበው ዘገባ ተስተካክሎና ታርሞ በክልሉ ፕሬዚዳንት በኩል እንዲቀርብለት አቶ ለማ መገርሳን ያሣሰበው ኢንሳ፤ የታገደበት መሬትም በእርሳቸው በኩል እንዲለቀቅለት ጠይቋል።
ኢንሳ የክልሉ ቴሌቪዥን በሠራው ፕሮግራም አለኝ የሚለውን ቅሬታ ለጣቢያው ማቅረብ ሲገባው፤ በክልሉ ፕሪዚዳንት በኩል መሄዱ ደብዳቤውን የተመለከቱ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ሲያነጋግር ውሏል።