የኢትዮጵያ የብድር ጫና በባለስልጣናት ዘንድ ጭንቀት እየፈጠረ ነው

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 26/2009)የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ በመምጣቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ጭንቀት መኖሩ ተጠቆመ።
እየጨመረ በመምጣቱ በባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀት የፈጠረው የኢትዮጵያ የብድር ጫና በአብዛኛው የተገኘው ከቻይና መንግስት ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ላይ የተቆለለው ከፍተኛ የብድር ጫና በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም/አይ ኤም ኤፍ/ ሳይቀር ሪፖርት መደረጉንም ዘገባዎች ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የብድር ጫና በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ በሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙሪያ ባሉ የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪዎችና ትልልቅ ባለስልጣናት ዘንድ ጭንቀትን ፈጥሯል።
ብድሩ ደግሞ ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት በመሆኑም የትኛው ትውልድ ከፍሎ ይጨርሰው ይሆን እያስባለ ነው።
ፎርቹን የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያ በቦንድ ሽያጭ ብቻ ከአውሮፓ ከተበደረችው 1 ቢሊየን ዶላር 6 ነጥብ 6 በመቶ የወለድ መጠን ትከፍላለች።
ይህም በቀጣዮቹ 10 አመታት ብቻ እየናረ ስለሚሄድ ከፍተኛ እዳ እንደሚያስከትል ነው የተገለጸው።
ከዚህ በተጨማሪም ሳውዲአረቢያ ወለድ አልባ ነው በሚል ለኢትዮጵያ ያበደረችውም በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ከፍተኛ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
ይህም ሁሉ ሆኖ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከቻይና የተበደረችው የእዳ ጫና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለስልጣናትን እያሳሰበ እንደሚገኝ ጋዜጣው ባቀረበው መረጃ ገልጿል።
ጭንቀት ውስጥ የገቡት ባለስልጣናትንም ፎርቹን በስም ጠቅሷቸዋል።እነዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፣የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር አቶ ይናገር ደሴና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ መኮንን ማንያዘዋል ናቸው።
ባለስልጣናቱ የሀገሪቱን ያለፉት አመታት የብድር ሁኔታ ሲገመግሙ የኢትዮጵያ የብድር ጫና በእጅጉ እያሻቀበ መሆኑን ተረድተዋል።
በግምገማቸው አማካይ ሀገራዊ ገቢን መሰረት በማድረግ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990 ከነበረው ጋር ብድሩ ሲነጻጸር በ150 ፐርሰንት መጨመሩን ተገንዝበዋል ነው የተባለው።
በተለይ ባለፈው አመት ብቻ ያለው ሁኔታ ሲታይ የብድር መጠኑ በ30 በመቶ በመጨመሩ ከፍተኛ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ለማወቅ ተችሏል።
ስልጣን ላይ ያለው የህወሃት አገዛዝ ግን የብድር ጫናው እንደማያሳስበውና ገንዘቡ አገልግሎት ላይ የዋለው በመሰረተ ልማት ላይ ነው በሚል እያስተባበለ እንደሆነ ተገልጿል።
በሙስና ተመዘበረ ስለተባለውና ባለፈው የ26 አመታት የአገዛዝ ጊዜ ከሀገር ወጥቷል የተባለው 30 ቢሊየን ዶላር ጉዳይ ግን ባለስልጣናቱን የሚያሳስብ አይደለም።