የኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነትና መረብ ኤጀንሲ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን አስኮ ከተባለ ኩባንያ ለመግዛት የ1.3 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ፈጸመ

ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2009)

መቀመጫውን በአውሮፓ ፖላንድ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ለኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነትና መረብ ኤጀንሲ የተለያዩ የኢንተርኔት የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ የ1.3 ሚሊዮን ዶላር (ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ) ስምምነት ፈጸመ።

አስኮ (ASSECO) ግሩፕ የሚል መጠሪያ ያለው ይኸው ኩባንያ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ሶፍትዌሮችን በማምረት ለተለያዩ ድርጅቶችና አገራት የሚያቀርብ እንደሆነ ኩባንያው በድረገጹ ላይ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ መረጃና ደህንነት መረብ ኤጀንሲ በደህንነት ስራዎች ላይ የሚያተኩር መንግስታዊ ተቋም ነው ሲል የገለጸው ኩባንያ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዘመናዊ ሶፍትዌሮችና ተያያዥ ቁሳቁሶች እንደሚቀርቡለት አመልክቷል።

ይሁንና የፖላንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ለኢትዮጵያ ሊያቀርብ ስምምነት ስለገባቸው የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለት አመት በፊት ከአንድ የጣሊያን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር ተመሳሳይ ስምምነትን በማድረግ የረቀቁ የኢንተርኔት የስለላ ድርጊቶችን ለመፈጸም የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ሲቀበል እንደነበር መጋለጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ቴክኖሎጂ ይጠቀም እንደነበር ያጋለጠው አንድ የካናዳ ሲቲዝን ላብ የተሰኘ ተቋም፣ ኢትዮጵያ አገልግሎቱን የተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የጋዜጠኞችን የግል የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ለመሰለል ትጠቀም እንደነበር በዝርዝር አመልክቷል።

የዚሁኑ መረጃ መውጣትን ተከትሎ አገልግሎቱን ሲያቀርብ የነበረው የጣሊያኑ ሃኪንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት የቴክኖሎጂ ግብዓቱን ከታለመለት አላማ ውጭ ለስለላ ተግባር አውሎታል ሲል ቅሬታን አቅርቦ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በወቅቱ ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

ይኸው የጣሊያን የቴክኖሎጂ ኩባንያ አገልግሎቱን ለማቅረብ በአንድ ወቅት የአንድ ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ የተቀበለበትን ደረሰኝ በማስረጃነት በማቅረብ ስምምነቱ ለህዝብ ግልጽ እንዲሆን አድርጓል።

የኢትዮጵያ የደህንነት አባላት ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ምክንያት ሊገለጡ እንደቻሉ ገልጾ የነበረው ይኸው የጣሊያን ኩባንያ፣ አገልግሎቱን እንዳቋረጠ በወቅቱ ይፋ ማድረጉንም ኢሳትና በርካታ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ መቆየታቸውም አይዘነጋም።

ከፖላንዱ ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ  የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው መረጃና ምላሽ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የኢንፎርሜሽን መረጃ ደህንነት ኤጀንሲ በሃገር አቀፍ ደረጃ የመረጃ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ የአሰራር ስርዓት ሰነድ መዘጋጀቱን ረቡዕ ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ አዲሱ አሰራር የመረብ ጥቃት ተጋላጭነትን ለመከላከል ያለመ እንደሆነ ለሃገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ይሁንና ሃላፊው ከፖላንድ ኩባንያ ስለተድረሰው ስምምነት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።