የኢትዮጵያ ወታደሮች ሁለት የሶማሊያ ተቃዋሚ መሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋሉ

ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በለድ-ዌይን በተባለዉ የማዕከላዊ ሶማሊያ ሂራን ክልል ዉስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ሁለት የሶማሊያ ተቃዋሚ መሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸዉን ኦጋዴን ቱዴይ የዜና ምንጭ ከናይሮቢ ገለፀ።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሶማሊያ የሽግግር መንግሰት ተባባሪ የሆነዉ የአህሉ ሱና ሱፊ ፓራ ሚሊቴሪ ቡድን መሪ አዳን አዋሌና ከፊል ራስ ገዝ የሆነዉ የሸበሌ ሸለቆ አስተዳዳሪ አብዱል ፈታህ ሃሰን ጃማ ናቸዉ።
መሪዎቹን የኢትዮጵያ መንግሰት ወታደሮች ያሰሯቸዉ የበለደ-ዌይን አካባቢ ለመቆጣጠር ከተደረገዉ ግጭት በሁዋላ እንደሆነ የዜና ምንጩ በተጨማሪ ገልጿል።
አንድ የሶማሊያ የፓርላማ አባል የኢትዮጵያ ወታደሮች የኢህሊሳ ዋል-ጀማን ሱፊ ወገን መደገፋቸዉ አግባብ እንዳልሆነ የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ ጦር አህሉ ሱና ዋል-ጀማን በፋይናንስና በስልጠና እንደሚረዳ በርካታ የሶማሊያ የፖለቲካ ሰዎች ይናገራሉ።
ጦሩ ይህንን የሚያደርገዉ ቡድኑ የተቆጣጠራቸዉን አካባቢዎች ነፃ ክልል አድርጎ የኢትዮጵያ ጦር ለመንቀሳቀስ እንዲያመቸዉ መሆኑን ኦጋዴን ቱዴይ በተጨማሪ ገልጿል።