የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ -ክርስቲያን ህንፃዎች ህገ-ወጥ ተብለው ፈረሱ

 ቤተ-ክርስቲያኒቱ ዳግማዊ ምኒልክ ፊት ለፊት በሚገኘው በተለምዶ ‹‹ጠጠር ሕንፃ›› በሚባለው ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ግንባታዎቿ ሕገወጥ እየተባሉ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን አጥብቃ ተቃወመች::

 የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር መሰንበቻውን በቤተክህነት ሕንፃ ላይ ባካሄደው ዘመቻ፤ አምስት የንግድ ቤቶችንና መጋዘኖችን

አፍርሷል::  እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤ ከቤተክህነት ቤቶቹንና መጋዘኖቹን ተከራይተው ይሠሩ የነበሩ ነጋዴዎች ወረዳው የወሰደውን ዕርምጃ ሕጋዊነት የሌለው ሲሉ ከቤተክህነት ጋር በመሆን እየተቃወሙት ይገኛሉ::

 ተቃውሞ በማሰማት ላይ የሚገኙት ድርጅቶችም፦ ሐረግ ካፌ፣ ዳሸን ምግብ ቤት፣ አዲስ ቢዝነስ ዩኒቲ፣ ፈቃዱ ፋንታዬ የጽሕፈት መሣርያ መደብርና

ዩኒቨርሳል ቤተ መጻሕፍት ናቸው::   እነዚህ የንግድ ሥራዎች የሚካሄዱባቸው ግንባታዎች “ሕገወጥ ግንባታዎች ናቸው” በሚል ነው ወረዳው ዕርምጃውን የወሰደው::

 በተወሰደው እርምጃ ግራ የተጋቡ በህንፃው ውስጥ የሚሰሩ ነጋዴዎች፦  “ሕገወጥ ማለት ምንድን ነው?” ሲሉ   ይጠይቃሉ::   ቤተክህነት  በደርግ መንግሥት የተወረሱባትን ሕንፃዎች በ አቶ መለስ ዜናዊ ፊርማ  በ1998 ዓ.ም. መልሳ ማግኘቷ ይታወሳል::

 ቤተክህነት በ አቶ መለስ ፊርማ  ከተረከበቻቸው ሕንፃዎች መካከል አንዱ ‹‹ጠጠር ሕንፃ›› ሲሆን፣ ከዚሁ ሕንፃ ጋር አሁን በወረዳው ሕገወጥ የተባሉ ግንባታዎችንም አብራ መረከቧን ሠራተኞቿ ይገልጻሉ::

 በህንፃዎቹ እየሠሩ ያሉ የንግድ ሰዎች ከቤተክህነት ጋር ሁከት ይወገድልኝ ሲሉ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር::  ይሁንና ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ፣ ወረዳው -የክስ ምክንያት የሆኑት ግንባታዎች እንዲስተካከሉ  መጠየቁና ማሸጉ፤ የተሰጠውን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት መወጣት እንጂ ሁከት መፍጠር አይደለም ሲል ወስኗል::

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሕግ ባለሙያ ሊቀ ጉባዔ ቀለመወርቅ

ውብነህ ፦”የአስተዳደሩ ፍርድ ቤት በክፍለ ከተማና በወረዳ ሥር ያለ ፍርድ ቤት ነው:: መሐንዲሶቹም በዚሁ መዋቅር ውስጥ ያሉ ናቸው:: ገለልተኛ አይደሉም:: ሁሉም ፤አንድ አካል ናቸው ፤ ገለልተኛ አካል ቢሆኑ፤ ግንባታው ሕገ-ወጥ እንዳልሆነ ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል፤››ሲሉ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል::

 በምርጫ 97 ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን፦”የነፍጠኞች መሸሸጊያ ዋሻ ሆኗል ”በማለት መናገራቸው አይዘነጋም።