የ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር የፃፉት ደብዳቤ ይፋ ሆነ

ጥር 30 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት ተከሰው የ 17 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረ-እግዚአብሔር የፃፉት ደብዳቤ ይፋ ሆነ። አቶ ዘሪሁን ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት በወረዱበት ቀን ለፍኖተ-ነፃነት አንድ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር ያወሳው የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል፤ ጉዳያቸው ገና በፍርድ ቤት እየታየ ስለነበር በወቅቱ ደብዳቤውን ሊያወጣው እንዳልቻለ በመጥቀስ፤በትናንትናው ዕትሙ ይፋ አድርጎታል።
አቶ ዘሪሁን በደብዳቤያቸው ላይ እንደገለፁት ፦ “በታሰርኩ በማግስቱ ምርመራ ቢሮ ተጠራሁ፡፡ ከዚያም መቼም አንተ የአራዳ ልጅ ነህ፡፡ እንደ ገጠር ልጅ አትገግምም፡፡እኛ በምንነግርህ መሠረት በመድረክ መሪዎች፣በ አንድነት ፓርቲ አመራሮችና በ ኤልያስ ክፍሌ ላይ ትመሰክራለህ፡፡ ከዚያም ትለቀቃለህ አሉኝ” ይላሉ።
“ምንድነው የምመሰክረው? ብዬ ስጠይቃቸውም.. በማለት ይቀጥላሉ አቶ ዘሪሁን “…ምንድነው የምመሰክረው ብዬ ስጠይቃቸውም-ሽብርተኞች ናቸው፡፡ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ይህን ይህን.. አድርገዋል፡፡ እኔንም እንዲህ እንዲህ.. አድርግ ብለውኛል ብለህ ትመሰክራለህ አሉኝ”ብለዋል።
በዚህን ጊዜ አቶ ዘሪሁን ለመርማሪዎቹ በሰጧቸው መልስ ፦”በእርግጥ መርካቶ ተወልጄ አድጌአለሁ፡፡ የአራዳ ልጅ ወይም የመርካቶ ልጅ አብሮ ይሰራል፡፡ አብሮ ተሻምቶና ተቀማምቶ ይበላል፡፡ ለጓደኛውና ለእውነት ይሞታል፤ እንጂ በማያውቀው ነገር የሐሰት ምስክር አይሆንም፡ የአራዳ ልጅ በእምነቱ ይሞታል እንጂ ግብዝ አይሆንም፡፡ እየሰማሁ ያደኩት ይህንን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔ በሐሰት አልመሰክርም፡፡ ማስረጃ አለን ብላችሁ ከያዛችሁኝ በኋላ እንዴት እንዲህ ትሉኛላችሁ?”በማለት ይናገራሉ፡፡
የኢብአፓ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን በመቀጠልም፦“በሰጠሁዋቸው ምላሽ የተበሳጩት መርማሪዎቹም ፦ፍ/ቤቱን የምናዘው እኛ ነን፡፡ እንቢ ካልክ የ20 ዓመት እስር ይጠብቅሀል፡፡የሚደርስብህን ሁሉ ታያለህ አሉኝ።እኔም የፈለጋችሁትን አምጡ እንጂ በሐሰት ምስክር ሆኜ አልቀርብም አልኳቸው”ብለዋል።
አቶ ዘሪሁን በዛቻና በማስራሪያ ብዛት ከአቋማቸው ሊነቃነቁ አለማቻላቸውን ያዩት መርማሪዎቹም ፊታቸውን ወደ ቤተሰቦቻቸው በማዞር ቀጣይ ሙከራ ማድረግ ጀመሩ።
፡የአቶ ዘሪሁን ቤተሰቦች ፦መርማሪ ፖሊስ ጠርቷቸው ፦”ምከሩት፡፡ ለሰው ብሎ ራሱንና ቤተሰቡን እየጐዳ ነው፡፡ እሱ እንዴት የቤተሰብ ኃላፊነት አይሰማውም? እኛ እሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን እሱ ግን እንቢ እያለ ነው፡፡ ቀላሉን ጉዳይ፤ ከባድ እያደረገው ነው፡፡ ብትመክሩት ይሻላል” እንዳላቸው ለፍኖተ-ነፃነት ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
ቤተሰቦቹም በየዋህነት ሄደው መርማሪው ፖሊስ ባለበት፦” ለምን የሚሉህን እሺ አትላቸውም? ይኽው መርማሪው ፖሊስ ምከሩት እያለን ነው፡፡ መፈታት አትፈልግም ወይ? ለእኛስ ለምን አታስብልንም?” በማለት ለመምከር ሲሞክሩ፤አቶ ዘሪሁን እዚያው መርማሪው ፖሊስ ፊት ፦” ምኑን ነው እሺ የምለው?” በማለት ንዴታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ባለቤታቸው ጋር ከፍ ያለ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ልጃቸው አባብላ ገላግላቸዋለች።
ምን እንዲያደርጉ እንደተጠየቁ ያልተረዱት ቤተሰቦቻቸውም ንዴታቸውን ሲመለከቱ፦”እኛ፤ እሱ ንገሩት ያለንን ነው እንዲሁ የነገርንህ፡፡ነገሩ ምን እንደሆነ የምናውቀው ምስጥር የለም፡፡ ሁሉንም የምታውቀው አንተ ነህ”በማለት እንዳረጋጓቸውና ከዚያ በኋላ ነገሩን አንስተውባቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ከዚህ በሁዋላ ነው በ አቶ ዘሪሁን ላይ ሀይል የታከለበት ምርመራ እንዲደረግባቸው የተወሰነው።
አቶ ዘሪሁን በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ይመላለሱ በነበረበት ወቅት፦ “ለሁለት ወር ጨለማ ቤት አስገብተው ለብቻዬ አሰሩኝ፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ ሰቅለው ሲቀጠቅጡኝ ውለው አደሩ፡፡ ጠባሳውን አሁንም ማሳየት እችላለሁ፡፡ ህክምናም እንዳላገኝ ተከለከልኩ”በማለት ለፍርድ ቤቱ መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህም ባሻገር ፦”ፍርድ ቤቱን የምናዘው እኛ ነን” ያሉት መርማሪዎች እንደዛቱባቸው አቶ ዘሪሁን የ 17 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

መምህርትና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በተመሣሳይ በሀሰት መስክራ እንድትፈታ በከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር የተነገራትን ማባበያና ማስፈራሪያ አልቀበልም በማለቷ የ14 ዓመት እስራትና የ 35 ሺህ ብር ቅጣት እንደተላለፈባት ይታወቃል።
አቶ ዘሪሁን የፃፉትን ሙሉ ደብዳቤ በቀጣይ ዕትሙ እንደሚያወጣው የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ገልጿል።