የኢትዮጵያ ሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና የቢሮ ሃላፊው በቅርቡ የሰጧቸው መግለጫዎች አፍራሽና ሕዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ናቸው ተባለ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 29/2010) የፌደራል መንግስት የኢትዮጵያ ሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና የቢሮ ሃላፊው በቅርቡ የሰጧቸው መግለጫዎች አፍራሽና ሕዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ናቸው በሚል ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በኦሮሚያ ጥቃት ላይ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተደረገ የጋራ መግለጫ በሚል ያወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚቃረን ነው።

እናም የሚመለከተው አካል ይህንኑ ጉዳይ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በሶማሌ ክልላዊ አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና በቢሮ ሃላፊው ላይ ያወጣው መግለጫ መረር ያለ ነው።

እንደ መግለጫው መስከረም 23/2010 በሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ድረገጽና በቢሮው ሃላፊ የተሰራጨው መረጃ የፌደራል ስርአቱን ከሚያራምድ ማንኛውም አመራር የማይጠበቅ ነው።

የሶማሌ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና የቢሮ ሃላፊው በፌስቡክ ድረገጻቸው ያወጡት መግለጫ አፍራሽና ሕዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል መረጃን የያዘ ነው ብሏል መግለጫው።

ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ መገናኛ ብዙሃን ከእንዲህ አይነቱ ድርጊት እንዲቆጠቡ በቅርቡ የሰጡትን መግለጫ የሚቃረን እንደሆነ ነው የገለጸው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከእንዲህ አይነቱ ድርጊት መገናኛ ብዙሃን እንዲርቁ ያወጣውን ማስጠንቀቂያም የጣሰ ነው ሲል መግለጫው አስጠንቅቋል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን መንግስት ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበርም አሳስቧል።

እናም ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን ጠቅሶ ሌላ ማስጠንቀቂያ ያወጣው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና በቢሮው ሃላፊ መስከረም 23/2010 የወጣውን ጽሁፍና መረጃ መርምሮ በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ዝቷል።

በሕገመንግስቱ አንቀጽ 29 መሰረት ሀሳብን የመግለጽ መብት መከበሩን ያስታወሰው መግለጫ በዚሁ ላይ ግን ጦርነትን የሚያባብሱ መግለጫዎች ገደብ እንደተጣለባቸው ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

የአሁኑ የመንግስት መግለጫ ያነጣጠረው በሶማሌ ክልል አስተዳደር ላይ ቢሆንም ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ነገር የለም።

በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት አሁንም አለመቆሙ ይነገራል።ይህንንም የመንግስት ኮሚኒኬሽኝ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አምነዋል።

ችግሩ የተባባሰው ግን በሁለቱ ክልሎች በሚሰጡ መግለጫዎች መሆኑን መንግስት እየገለጸ ይገኛል።

የሶማሌ ክልላዊ አስተዳደር በፌደራሉ የወጣውን የማስጠንቀቂያ መግለጫ ተከትሎ እስካሁን ያለው ነገር የለም።