የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት ለለውጥ ከሚታገሉ ከማናቸውም ሃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 24/2009)የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት ኢትዮጵያ ውስጥ ለለውጥ ከሚታገሉ ከማናቸውም ሃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ንቅናቄው ይህን ያስታወቀው 3ኛውን አመታዊ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ ባካሄደበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት 3ኛው አመታዊ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄዷል።
ህብረቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሀምሌ 29ና 30 ባደረገው አመታዊ ጉባኤ የአመታዊ አፈጻጸም ሪፖርቱን አዳምጧል።
በማስከተልም ተጋባዥ እንግዶች በንቅናቄው የትላንትና የሚቀጥሉት ጉዞዎች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎችን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት ጸሃፊ አቶ ኡመር ሺፋ ባቀረቡት አመታዊ ሪፖርት ህብረቱ ከተለያዩ የለውጥ ፈላጊዎች ጋር በአንድነት ተጣምሮ ለመስራት ባደረገው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ልዩነታቸውን በማጥበብ ዋነኛ ጠላታቸው የሆነውን አገዛዝ በጋራ ለመታገል የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ከጎናቸው መሰለፋቸውን ለጉባኤው ገልጸዋል።
በተለይም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ወደ ተግባር ከገባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ከዲሲ ግብረሃይል፣በ8 ድርጅቶች በተፈጠረው የቀውጢ ጊዜ አገር አድን ግብረ ሃይል፣ከዲሲ ኦሮሞ ሙስሊም ፋውንዴሽንና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በአንድነትና ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት 3ኛ አመታዊ ጉባኤ ላይ ከተጋበዙት የፖለቲካ መሪዎች አንዱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ዶክተር አዚዝ አህመድ፣የህግ ባለሙያው ዶክተር አባድር ኢብራሂም፣ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ፣የኢሳት ባልደረባ አቶ ኤርሚያስ ለገሰና የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው በህብረቱ እንቅስቃሴዎችና ቀጣይ መሆን ያለባቸው በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ንግግራቸውን አሰምተዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ህብረት በሚያደረገው እንቅስቃሴ ከጎኔ አልተለዩም በማለት ለጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ፣ለአቶ ሀብታሙ አያሌው፣ለዶክተር አባድር ኢብራሂም፣ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን(ኢሳት)፣ለጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ፣ለዶክተር አወል አሎና ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የእውቅና ሽልማት አበርክተዋል።