የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከ720 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስታዲየም እያስገነባ ነው

የካቲት ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለቀጣዩ ዓመት የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ተረኛ አዘጋጅነት የተመረጠው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከ720 ሚሊየን ብር በላይ በማውጣት በሰመራ ከተማ 30 ሺ ሕዝብ የሚይዝ ዘመናዊ ስታዲየም እያስገነባ ነው።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ድርቅ ከተጠቁ ክልሎች ቀዳሚ የሆነው የአፋር ክልል ፣ አሁንም ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ በድርቁ እየተጎዳ ባለበት ሰአት የሚያስገነባውን ስታዲየም እስከመጪው ዓመት ህዳር ወር ድረስ ቢያንስ ለበዓሉ ማከናወኛ የሚረዳውን ሥራ በአጣዳፊ ሁኔታ እንዲከናወን ውል ያሰረ ሲሆን፣ የግንባታው ሙሉ ስራ የሚጠናቀቀው በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ተብሎአል፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነው የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በተለየ ሁኔታ በማግኘት በተመሠረተ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ቢሊየነር መሆን የቻለውና በየክልሉ የሚገነቡ የብሄር ብሄረሰቦችን ስታዲየም የሚገነባው ከህወሃት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው «አፍሮ ጽዮን» የሚባለው የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፡፡
ለብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል በዓል ለእንግዶች አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችን ጨምሮ ሌሎች ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎችን የመገንባቱ ስራም ከዚህ ጎን ለጎን እየተካሄደ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዓመታዊ በዓል ለማክበር ክልሎች በእያመቱ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚያወጡ ይታወቃል፡፡