የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተወካይ መርካቶ ውጥንቅጡ እንደወጣና በአስፈሪ ጎዳና ላይ መገኘቱንና ተናገሩ

 

ታህሳስ 28 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተወካይ  መርካቶ ውጥንቅጡ እንደወጣና በአስፈሪ ጎዳና ላይ መገኘቱንና ፣ ‹‹ነጋዴው ታግሶና ቆሞ ያለው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው›› መሆኑን ተናገሩ

 

ተወካዩ ይህን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም የንግድ ምክር ቤት የሥራ አመራርና አባላትን፣ እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች ተወካዮችን በአስተዳደሩ የባህል አዳራሽ በሊዝ አዋጁ ዙሪያ ባወያየበት ወቅት ነው
ውይይቱን የመሩት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ የከተማው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍስሐና የከንቲባው ልዩ አማካሪ አቶ ጌታቸው አምባዬ ነበሩ፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ኩማ፣ አዋጁ ዋናው ያስፈለገበት ምክንያት ፈጣንና የማያቋርጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና ብዙኅኑን የዕድገቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን አብራርተው፣ መድረኩን ለውይይት ክፍት አደርገዋል፡፡

ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የተወከሉ እንደገለጹት፣ ከመንግሥት በተሰጣቸው ፈቃድ ተደራጅተው 100 ሚሊዮን ብር በማሳየት ከ1996 ዓ.ም ጀምረው በራሳቸው ይዞታ ላይ ለማልማት መሬት ቢጠይቁ፣ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር እስካሁን ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ እሳቸው አባል የሆኑበት በአክሲዮን የተደራጀ ማኅበር 50 ሚሊዮን ብር አስይዞ ቢጠይቅም ሲገፋ መቆየቱን ተናግረው፣ ከአንድ ወር በፊት ‹‹አስጠንታችሁ ያቀረባችሁትን ኤልዲፒ ውሰዱ›› በመባላቸው፣ የመርካቶ ነጋዴ ‹‹ለካ ሲገፋን ሲገፋን እዚህ ያደረሰን ይዞታችንን በዚህ አዋጅ ለመንጠቅ ነው፤›› በማለት አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡
መርካቶ ውጥንቅጡ እንደወጣና በአስፈሪ ጎዳና ላይ መሆኑን የገለጹት ተወካዩዋ፣ ‹‹ነጋዴው ታግሶና ቆሞ ያለው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው›› ካሉ በኋላ ከንቲባውን ጨምሮ ሁሉም ባለሥልጣናት የታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ወርደው እንዲያነጋግሩ ለምነዋል፡፡

ሪፖርትር እንደዘገበው አዋጁ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተቃውሞ እንደገጠመውና አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከነዋሪውና ከልዩ ልዩ ባለሙያዎች ጋር በመወያየት አስተያየት ተሰጥቶበት ፀድቆ ቢወጣ የተሻለና ተቀባይነት ያለው አዋጅ ይሆን እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የንግድ ምክር ቤት ተወካይ ሲሆኑ፣ አዋጁ አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾች እንዳሉበትና በተለይ የአማርኛውና የእንግሊዝኛው ትርጉም ‹‹የውጫሌን ውል ያስታውሰኛል›› በማለት አለመገናኘቱን አስታውቀዋል፡፡
አዋጁ ያለውይይት በድብቅ የፀደቀው መንግሥት ለጀመረው መጠነ ሰፊ የልማት ፅቅድ ማስፈፀሚያ ገንዘብ ለማግኘት መሆኑን የሚገልጹ እንዳሉ የተናገሩት ተወካዩ፣ ይህ እውነት ከሆነ ‹‹መንግሥት ገንዘብ ያስፈልገኛል ብሎ የማይሆን አዋጅ መውጣት አልነበረበትም፤›› ብለዋል፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ካስፈለገ እንደ ኤግዚቢሽን ማዕከል ዓይነት ቦታዎችን በማዘጋጀትና በሊዝ በማከራየት ገቢ ማግኘት እንደሚችልም ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
ከልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የመጡ ተወካይ እንደገለጹት፣ የከተማ ቦታና የገጠር መሬት አዋጅ መነሻው በጥቂት ከበርቴዎች የተያዘን መሬት ለብዙኀኑ ለማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም እስከ 500 ካሬ ሜትር ለሕዝቡ ተሰጥቷል፡፡ በተለይ በከተማ አካባቢ በነፃ መሬት ተሰጥቷል፡፡ አሁን ግን ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ይዛወር መባሉ አግባብ አይደለም፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላ መወያየቱ ፋይዳ የለውም እንጂ ቢሻሻል ጥሩ ነበር በማለት ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የተወከሉ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ፣ አዋጁ ብዙኀኑን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ (3) የተሰጠን መብት የሚደግፍ፣ የሀብት ክፍፍል በእኩልነት ለማራመድ የሚያደርግ መሆኑንና ኢሕአዴግ እስካሁን የሠራቸውን የመንገድ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶችንና ሌሎች ልማቶችን በማድነቅ አስተያየት ከሰጡ በኋላ፤ ‹‹አሁን መንግሥት እንዲያደርግ የምንፈልገው የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ ያልተመዘገቡ ዜጎች እንዲመዘገቡ እንዲያደርግ ብቻ ነው፤›› ብለዋል።

አንድ ከግሉ ዘርፍ የመጣሁ ነኝ ያሉ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ዛሬ የተጠራነው ነባር ይዞታን በሊዝ ስለማስተላለፍ የወጣውን አዋጅ በሚመለከት ለመወያየት ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ሕዝቡ በአዋጁ ላይ ያለውን ቅሬታ ተናግረው፣ ከየክፍለ ከተማው ተወከልን የሚሉትና ድጋፋቸውን የሰጡት ውይይቱን ለማድበስበስ እየሞከሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በላይ ተቀምጠው የቆዩ ፋይሎች እየተመዘዙ እየተመራባቸው እንደሚገኝ በመጠቆም፣ ‹‹የእኛ ሰው በመሬቱና በሚስቱ ሲመጡበት ምን እንደሚሆን እየታወቀ፣ የውይይቱን መንፈስ የሳተ ነጥብ በማንሳት ‹‹መንገድ ተሠርቷል፣ ኮንዶሚኒየም ተገንብቷል፤›› ማለቱ ለማንም የሚጠቅም አለመሆኑንና ሁሉም የሚያውቀው መሆኑን በመጠቆም ወደ ቁምነገሩ መመለስ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

አዋጁን ሲመለከቱት መንግሥት ከሚከተለው ፖሊሲ አንፃር ብዙ መነጋገር እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ ጠበቃ ሞላ ዘገዬ ሲሆኑ፣ የተገኙት የንግዱን ማኅበረሰብ በመወከል መሆኑን ተናግረው በሰጡት አስተያየት፣ ተደጋግሞ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው የሚባለው አነጋገር በአዋጁ 47/67 የተደነገገ መሆኑንና የብዙዎችን ባለይዞታነት የሚነፍግ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋናው ነገር ግን አዲሱ አዋጅ ባለይዞታ ሊሸጥ ሲፈልግ ገዢው በሊዝ ስለሚገዛ ገዢ ‹‹ለምን ይኼንን ያህል አወጣለሁ›› እንደሚል፣ ሻጭ ደግሞ ‹‹ንብረቴ ዋጋው ቀንሷል›› በሚል በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
የፊሊንትስቶን ባለቤት አቶ ፀደቀ ይሁኔ አዋጁን እንዳነበቡትና በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ምሳሌዎችንና መረጃዎችን በማስደገፍ ማብራርያ ሰጥተው፣ ኅብረተሰቡ አዋጁ ስላላነበበና ግንዛቤ ስላጣው ተቃውሞ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ መሬት ሲሸጥ ወደ ሊዝ እንደሚዛወር የሚገልጽ መሆኑን በማስታወስ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት አቶ ፀደቀ፣ 95 በመቶ መንግሥት ሊወስደው ነው የሚለውን ግንዛቤ በመስፋፋቱ ገበያቸው መቀዝቀዙንና እየተጎዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፈጣን ዕድገት ሲመዘገብ የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ አብሮ ካልተለወጠ አደጋ እንዳለው በመናገር፣ አዋጁን አለማንበብና አለማወቅ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ውይይቱ በየሴክተሩ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ መንግሥት የተለያዩ ግብዓቶችን ለማግኘት ይረዳው እንደነበር በመግለጽ፣ በዕለቱ የተገኙት የውይይቱ ታዳሚዎች የመጡት ስለ አዋጁ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አስረጂዎችን ለማግኘት ሳይሆን፣ አዋጁ የሚመለከተው አካል መልስ እንዲሰጥበት መሆኑን አንድ የንግድ ምክር ቤት ተወካይ በመግለጽ፣ የፍሊንትስቶን ባለቤት የሰጡትን አስተያየት አጣጥለውታል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ  የአዋጁ ረቂቅ ሲወጣ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ተደርጎበት ቢሆን ኖሮ ጥሩ እንደነበር አምነው፣ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሕዝቡን ስለሚወክሉ ተወያይተውበት አዋጁ መፅደቁን ተናግረዋል፡፡