የአዲስ አበባ አስተዳደር ለ2010 ካጸደቀው የ40 ቢሊየን ብር በጀት 30 ቢሊየኑን ከግብርና ከገቢ ሊሰበስብ ነው

(ኢሳት ዜናሐምሌ 14/2009)የአዲስ አበባ አስተዳደር በተጠናቀቀው የበጀት አመት ብቻ ከአንድ ከአንድ ቢሊየን አራት መቶ ሚሊየን ብር በላይ አባክኗል።

ይህም በዋና ኦዲተር ቢሮው ተረጋግጦ ብክነቱ በታየባቸው መስሪያ ቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዛቱ ይታወቃል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለቀጣዩ 2010 ባጸደቀው በጀት 40 ቢሊየን ብር ለካፒታልና መደበኛ በጀት ቢመድብም አብዛኛው እቅድ ግን ባልተጨበጠ ገንዘብና ገና ለገና ከግብርና ከገቢ የሚሰበሰብ ነው።

በአስተዳደሩ በጀት ላይ እንደተመለከተው ከአመታዊውና ቀጣይ በጀት ተብሎ ከተመደበው 40 ቢሊየን ብር 30 ቢሊየኑ ከግብርና ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ የተቀደ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አስተዳደሩ ይህንን ገቢ ለማሰባሰብ ያቀደው ከከተማው የመሬት ሊዝና ከግብር ጋር የተያያዘ ሆኗል።

በዚሁም ምክንያት በአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ይዞታቸው በሊዝ እንደሚሸጥ መገለጹን የኢሳት ምንጮች አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ በሰሞኑ ይፋ የተደረገው የቀን ገቢ ገብር ግምት የበዛውና ነዋሪዎችን ያስመረረውም አስተዳደሩ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን በህብረተሰቡ ላይ ጫና በማድረጉ መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ የቀን ገቢ ግብር በነዋሪዎች ላይ ከተጣለ በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች መደብሮችንና ሱቆችን በመዝጋት አመጽ መጀመራቸው ይታወሳል።

አመጹ በኮልፌ፣አጣና ተራ፣አስኮ፣ብሔረ ጽጌና በከፊል መርካቶ መታየቱን ዘገባዎቻችን አመልክተዋል።