የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከሀላፊነታቸው የተነሱት፦”ብቃት ስለሌላቸው” ነው ሲሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ

ኢሳት ዜና፡- ብአዴኖች በህወሀት ክፍፍል ወቅት ለአቶ መለስ ቡድን ታማኝነታቸውን በማሳየታቸው ምክንያት በሹመት በተንበሸበሹበት ወቅት ነው- የብአዴኑ አቶ ከፍያለው አዘዘ- ከመንግስት ጋዜጠኝነት ተነስተው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት።

ለረዥም ጊዜ  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የቆዩት አቶ ከፍያለው አዘዘ በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው ካቤኔ አዲስ አበባን ማስተዳደር ሲጀምር  የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተመደቡ።

ይሁንና አቶ አዲሱ ለገሰን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋን፣ ወይዘሮ ገነት ዘውዴን፣ አቶ ዳዊት ዮሀንስን፣ አቶ ህላዊ ዮሴፍንና ሌሎች ከፍተኛ የብአዴን አመራሮችን በተለያዬ መንገድ እንደገና ከስልጣን የመግፋቱና የማግለሉ  እርምጃ በስፋት መቀጠሉን ራሳቸው የብአዴን ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ።

 የማግለል እርምጃው ብአዴን፦”ተተኪዬ ናቸው”ብሎ ወዳዘጋጃቸው አባላቱ ጭምር መውረዱን የሚናገሩት እነዚሁ ወገኖች፤ያለ ህወሀት ሹሞች ትዕዛዝ የሚሰራ አንዳችም ነገር በሌለበት አገር ፤ በአዲስ አበባ ለተፈጠረው አስተዳደራዊ ቀውስና ህዝባዊ ብሶት፤አንድና ሁለት ሰዎችን የግንባር ስጋ አድርጎ ማቅረብ ሲበዛ ነውር ነው ይላሉ። 

ከ10 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ጎልቶ እየወጣ ለነበረው የህዝብ ብሶት ኢህአዴግ የወቅቱን ከንቲባ አቶ አሊ አብዶን  በመቸንከርና በግምገማ ላይ፦”በመዲናይቱ ለተፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጠያቂው እኔ ነኝ” ብለው እንዲናዘዙ በማድረግ -ጉዳዬ በብዙሀን መገናኛዎች እንዲሠራጭ ማድረጉ ይታወሳል። 

በወቅቱ አንዳንድ አፍቃሬ ኢህአዴግ ጋዜጦች ሳይቀሩ በአዲስ አበባ መስተዳድር ላይ  ፦”ዘመቻ ፀሀይ ግባት”  በማወጅና  ለአስተዳደራዊ ቀውሱ  ተጠያቂው የአቶ አሊ አብዶ አመራር ብቻ  እንደሆነ በማስመሰል፤ ህዝቡ የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ እንዳያስተውል ለገዥው ፓርቲ ሽፋን መስጠታቸው አይዘነጋም።

አቶ አሊ አብዶ በውርደት ስልጣናቸውን ለአቶ አርከበ ዕቁባይ ካስረከቡ ከወራት በሁዋላ በወቅቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ በረከት ስምዖን፤በደብረ-ዘይት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ለፌዴራል መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ፦ “ የአዲስ አበባ ችግር እንደ ድርጅት ሁላችንም የምንጠየቅበት ሆኖ ሳለ፤ አሊን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መስቀሉን እንዲሸከም አድርገነዋል” በማለት ተናገሩ-ከሰልጣኞቹ አንዱ የነበሩና አሁን በስደት የሚገኙ ግለሰብ እንዳታወሱት። 

አቶ አሊ አብዶ “ብቃት የለኝም፤ ጥፋቱ የኔ ነው”ብለው በውርደት ሲባረሩ ግምገማው ለመገናኛ ብዙሀን ክፍት የነበረ ሲሆን፤ አቶ በረከት “ጥፋቱ የሁላችንም ነው። አሊን ብቻ መስቀል ማሸከማችን ትክክል አይደለም”ብለው የተናገሩት ግን፤ ጋዜጠኞች ባልተገኙበት ዝግ ስልጠና ላይ ነው።

 እነሆ ከአስር ኣመት በሁዋላ በአዲስ አበባ ውስጥ ጎልቶና አገርሽቶ እየወጣ ነው ለተባለው ብሶት የብአዴኑ አቶ ከፍያለው አዘዘ  እንደአቶ አሊ አብዶ  መስቀሉን ይሸከሙ ዘንድ ተፈርዶባቸዋል። 

በግምገማው አዳራሽ  ፦“አቶ ከፍያለው ብቃት የላቸውም። ከተሰጣቸው ስራ አሻግረው ሌላ ነገር የመስራት ሀሳብና ተነሳሽነት የላቸውም፤ የተሰጣቸውንም ስራ ቢሆን በትክክል ለማጠናቀቅ የአቅም ችግር አለባቸው”ተብለው ሲብጠለጠሉ የተቀረፀው   ቪዲዮ፤ልክ እንደ ያኔው አቶ አሊ አብዶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና እወጃ  እንዲተላፍ ሆኗል። አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድም በተመሳሳይ መንገድ የቀድሞ አለቃቸውን ወርፈዋል። በዚሁ ግምገማ ሌላ አስገራሚ ሹም ሽርም ታይቷል።

በደሴ መምህራን ማሰልጠኛ በሌክቸረርነት ሲያገለግሉ ከነበሩበት ተነስተው የአማራ ክልል ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ሀላፊ ሆነው የተሾሙት የብአዴኑ አቶ ታቦር ገብረ-መድህን-በህወሀት ክፍፍል ማግስት እንደሌሎች የብአዴን ጓደኞቻቸው ሁሉ በአቶ አሰፋ በቀለ ምትክ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ።  ሆኖም እነሆ በሰሞኑ ግምገማ ከቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅነታቸው ተነስተውና፤የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክትል አፈ-ጉባኤ ተብለው ዝቅ ወዳለ ቦታ ተመድበዋል። የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደው በዚሁ የሹም ሽር ግምገማ ከዚህም በተጨማሪ በሚያሽከረክሩት መኪና ሰው በመግጨት ወንጀል ይፈለጋሉ ያላቸውን የምክር ቤቱን አባል  የአቶ ውብሸት ገብረ-እግዚአብሔርን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

በተለዬ መልኩ ብአዴኖችን መመንጠር ላይ ባተኮረ በሚመስለው በሰሞኑ የኢህአዴግ ግምገማ፤የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ልዑል ሰገድ ይፍሩ እና አንድ የአራዳ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ እንደተባረሩ መዘገባችን ይታወሳል።  

ከኃላፊነታቸው የተነሱት የኢህአዴግ አመራር አባላት፤ “ተከሰተ” ለተባለው ሁኔታ ተጠያቂ የተደረጉ ሲሆን፤ አሁን ፓርቲው እየወሰደው ባለው የእሳት ማጥፋት እንቅስቃሴ ውስጥ ትጋት ያልታየባቸውና መመሪያውን ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ያልታመነባቸው ናቸው ተብሏል።

ኢህአዴግ በቅርቡ ባደረገው የከፍተኛ አመራር ግምገማ ላይ፤ በአዲስ አበባ “የ1997 ዓ.ም ዓይነት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ” በማለት የዳሰሳ ምልከታ ከማቅረብ አልፎ፤ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ በትጋት ለመሥራትና ድባቡን ለመቀየር ፤ከዲፕሎማ በላይ በመማር ላይ የሚገኙ አባላቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ከወዲሁ ለምርጫው እንዲሰሩ ማዘዙ ይታወሳል፡፡ 

ይሁንና በተለያዩ መድረኮች በተደረጉ ግምገማዎች በተለየ መልኩ ለተፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የብአዴን ሹመኞች ተጠያቂ እየሆኑ ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው፤ ብአዴን በአቶ መለስ  እምነት እንዳጣና ጥርስ ውስጥ ሳይገባ እንዳልቀረ የሚያመለክት ነው ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች። 

በተለይም አቶ ከፍያለውንና አቶ ታቦርን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በግምገማ ከያዙት ቦታ እየተነሱ ያሉት በሙሉ፤ በህወሀት ክፍፍል ማግስት በአቶ በረከት ስምዖን መልማይነትና አቅራቢነት የተሾሙ ብአዴኖች መሆናቸው፤ በከፍተኛዎቹ የኢህአዴግ ሰዎች መካከል የእርስበርስ ጥርጣሬ መንገሱን የሚጠቁም ነው ይላሉ። 

የአቶ በረከት የቅርብ ሰው እና የዳሸን ቢራ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ብርሀኑ ዓለሙ፤ ከወራት በፊት የሙስና ክስ ተመስርቶባቸውና የ 18 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ወደ ቃሊቲ መውረዳቸው ይታወሳል።