የአዲስ አበባ መምህራን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቅርቡ የተደረገውን የደሞዝ ጭማሪ የተቃወሙ መምህራን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ውይይት መጀመራቸው ታውቋል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህር እንዳሉት መምህራን አሁን የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም መሰረታዊ የሚባል የደሞዝ ጭማሪ የጠየቁ ቢሆንም፣ መንግስት የሰጠው መልስ ግን መምህራንን ለበለጠ ጉዳት የሚዳርግ ነው። የኑሮ ውድነቱ ብቻውን መምህራን ለተቃውሞ እንዲነሱ አድርጓቸዋል ያሉት መምህሩ፣ ይህም በመሆኑ መምህራን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እና የተደረገውን የደሞዝ ጭማሪ ለመቃወም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከመምህራን ስሜት ውጭ በሆነ መልኩ የደሞዝ ጨማሪው የመምህራንን ፍላጎት ያረካነው በሚል የሰጠው መግለጫ መምህራን ተቃውሞውን በራሳቸው መንገድ ለማድረግ እየገፋፋቸው መሆኑን አክለዋል። የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ፍላጎት ቢኖርም እስካሁን ድረስ በምን መልኩና መቼ እንደሚደረግ የተወቀ ነገር አለመኖሩን፣ ይሁን እንጅ ውይይቶች መቀጠላቸውን መምህሩ ለኢሳት ገልጠዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት መምህራን ተቃውሞ እንዳያደርጉ እያስፈራሩና እያስጠነቀቁ መሆኑን መምህሩ ገልጠዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide