የአውሮፓ ህብረት 39 የፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ የሚፈጸመው የሰባዊ መብት ጥሰት እንዲጣራ ጥሪ አቀረቡ

ኢሳት ዜና ( ሃምሌ 4, 2009 ) የአውሮፓ ህብረት 39 የፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ የሚፈጸመው የሰባዊ መብት ጥሰት እንዲጣራ ጥሪ አቀረቡ ።

የፓርላማ አባላቱ የፈረሙት ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ያለው የሰባዊ መብት ረገጣ ሙሉ በሙሉ መጣራት ይኖርበታል ።በአገዛዙ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰባዊ መብት ኮሚሽን ተካሄደ የተባለው የምርመራ ሪፖርት የገለልተኛነት ጥያቄ እንዳለበትም የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል ።

የአውሮፓ ህብረት የ39ኙ የፓርላማ አባላት ፊርማ ያለበት ደብዳቤ የተላከው ለምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ ለሆኑት ፌድሪካ ሞግሄርኒ መሆኑ ታውቋል ።እናም የፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያ በሃገሪቱ ያለው የሰባዊ አያያዝ ሁኔታ ገለልተኛ አካል እንዳያጣራ መከልከሉ በቸልታ ሊታይ አይገባም ባይ ናቸው ። ገለልተኛ አጣሪ አካል ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሁኔታውን ካልመረመረ ባለፈው አንድ አመት በነበረው ህዝባዊ አመጽ የተገደሉትንና ደብዛቸው የጠፋ ሰዎችን ቁጥር በውል ማወቅ አይቻልም ነው ያሉት ። የፓርላማ አካላቱ እንደ አውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ገለጻ የኢትዮጵያ መንግስት ለፈጸማቸው ማናቸውም የሰባዊ መብት መተላለፍ ተጠያቂነትንና ሃላፊነትን መውሰድ ይኖርበታል ።

በሰባዊ መብት ረገጣው ሴቶች መደፈራቸውና የጾታ ጥቃት መፈጸሙንም የፓርላማ አባላቱ መረጃ እንዳላቸው አረጋግጠዋል ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከህግ ውጪ የተያዘበት መንገድና የእስር ሁኔታም በእጅጉ የሚያሳስባቸው ጉዳይ መሆኑንም 39ኙ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በደብዳቤቸው አጽኖት ሰጥተዋል ።

ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የእርዳታ ገንዘብ የምታገኘው ኢትዮጵያ የሰባዊ መብት የማታከብር ከሆነ ጉዳዩ እንደገና ሊጤንና ሃገሪቱ የምታገኘው ድጋፍ መገታት እንዳለበት የፓርላማ አባላቱ ጥሪ አቅርበዋል ። በኢትዮጵያ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስካሁን እንዳልተነሳና ሃገሪቱ አሁንም በውጥረት ውስጥ መሆኗንም አፍሪካ ታይምስ መግለጫውን መነሻ በማድረግ ዘገባ አቅርቧል ።