የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ በቂ ትኩረትን አልሰጡም ሲል ሂውማን ራይትስ ገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2009)

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት በሃገሪቱ በመፈጸም ላይ ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በቂ ትኩረትን አልሰጡም ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ለህብረቱ የቅሬታ ደብዳቤን አቀረበ።

በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት ባለ ትብብርና ግንኙነት ዙሪያ ለመምከር በአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚደንት ፊዴሪካ ሞገሪኒ የተመራ የልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ሰሞኑን ጉብኝትን ማድረጉ ይታወሳል። ይሁንና የልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ በሃገሪቱ በመፈጸም ላይ ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ስጋቱን አለመግለፁና በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ ጥሪ አለመቅረቡ አግባብ አለመሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለህብረቱ በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል።

ባለስልጣናቱ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ሚዛናዊ ያልሆነ ገለጻን አድርገዋል ሲል ተቃውሞን ያቀረበው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በሃገሪቱ ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ የሚወስዱ አፈናዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳይካተቱ መቅረታቸውን ገልጸዋል። የሁለቱ ወገኖች ምክክር በሰደተኞች፣ በኢኮኖሚያዊ እድገትና በሰብዓዊ ዕርዳታዎች ዙሪያ ብቻ ማተኮር ስጋት ማሳደሩን ድርጅቱ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ መንግስት በፈጸመው ላይ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሃገሪቱ የስደተኞችንና የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል ሲሉ በሂውማን ራይትስ ዎች የአውሮፓ ህብረት ዳይሬክተር የሆኑት ሎቴ ሌችት  ለህብረቱ ባቀረቡት ደብዳቤ አመልክተዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት የቢዝነስ መድረክ ለማካሄድ የያዙት ቀጠሮም በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከሚነሳ ድረስ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ የዜጎችን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እያባባሰ ባለበት ወቅት የአውሮፓ ህብረት ይህንኑ ጉዳት ወደጎን በመተው በቢዝነስ ትብብር ላይ ለመምከር አጀንዳ መያዙ ተገቢ አለመሆኑን ሂውማን ራይስት ዎች አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዲህ ያሉ ውይይቶችን ለማድረግ በሃገሪቱ መንግስት ባልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ላይ ከአመታት በፊት የወጡ እገዳዎችና መመሪያዎች ሊነሱና ማሻሻያዎች ሊደረግባቸው እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመኮነን የአውሮፓ ህብረት ሊወስዳቸው ይገባል ብሎ ያቀረባቸው ውሳኔ ሃሳቦች በህብረቱ በቂ ትኩረት ሳያገኙ መቅረቱንም ሂውማን ራይትስ ዎች ለህብረቱ በጻፈው ደብዳቤ አስፍሯል።

ህብረቱ ውሳኔዎቹን ችላ ብሎ መቆየቱ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተሳሳተ መልዕክትን ሊያስተላለፍ ይችላል ሲል ድርጅቱ ስጋቱን አክሎ ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያካሄዳቸው የጋራ ውይይቶች ዶ/ር መረራ ጉዲና አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ ማድረግ እንደሚገባውም ሂውማን ራይትስ ዎች ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚደንትና ለውጭ ጉዳዮች ተወካዮች በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል።

የአውሮፓ ህብረት ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው ስምምነት ሊደረስበት ባልቻለው የመንግስት የተወሰኑ የተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ሊካሄድ ለታቀደ ድርድር ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ኮንኗል።

መንግስት አካሄዷል የሚለው ድርድር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሌሎችን ማካተት ይኖርበታል ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች የአውሮፓ ህብረት ድጋፍን ተቃውሟል።

ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ከተወሰኑ ተቃዋሚዎች ጋር አካሄደዋለሁ ብሎ የነበረው ድርድር አለመግባባትን ፈጥሮ በቀጠሮ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።