የአቶ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ እንደሚፈጸም ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 16 ፥ 2009)

ታዋቂው ጸሃፊ፣ የህግ ባለሙያና የቀድሞ የፓርላማ አባል የአቶ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነስርዓት በትውልድ ሃገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚፈጸም ተገለጸ። አስከሬኑን ወደ ኢትዮጵያ ለመሸኘትም እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

እሁድ ሚያዚያ 15 ፥ 2009 በዬስ አሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ ህይወታቸው ያለፈው አቶ አሰፋ ጫቦ፣ ከ73 አመታት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞጎፋ ጨንቻ ከተማ መወለዳቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው የተከታተሉት አቶ አሰፋ ጫቦ፣ በህግ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል በዩ ኤስ አሜሪካ በተካሄደ የአለም አቀፍ ህግ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ከተገኙት ሶስቱ ኢትዮጵያውያን አንዱ የነበሩት አቶ አሰፋ ጫቦ ከጓደኞቹ ጋር በአንደኛነት በማሸነፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከቀዳማዊ ህይለ ስላሴ እጅ የወርቅ ሰዓት መሸለማቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በአብዮቱ አፍላ ወቅት በፖለቲካው ትግል ተሳታፊ የነበሩት አቶ አሰፋ ጫቦ በደርግ ስርዓት 11 አመታት በእስር ቤት ቆይተዋል። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በሽግግሩ መንግስት ተሳታፊና የም/ቤት አባል ነበሩ። ሆኖም በአፍላው የሽግግሩን ሂደት አካሄድ በመቃወም ራሳቸውን ከም/ቤት በማግለል የተሰደዱት አቶ አሰፋ ጫቦ ላለፉት 24 አመታት ያህል በዩ ኤስ አሜሪካ በስደት ቆይተዋል።

የአራት ልጆች አባትና የዘጠኝ ልጆች አያት የነበሩት የአቶ አሰፋ ጫቦ ቀብር በኢትዮጵያ የሚፈጸም ሲሆን፣ የመሸኘቱ እንቅስቃሴም ተጀምሯል።

ኢትዮጵያውያን ለቀብሩ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ከዚህ በታች የሚገኘውን ሊንክ በመጫን እንዲለግሱ ጥሪ ቀርቧል።

https://www.gofundme.com/assefa-chabo?ssid=984708092&pos=1