የአቶ መለስ ዜናዊ አያት የባሻ አስረስ ተሰማ ፎቶ ግራፍ በፌስ ቡክ እየተሰራጨ ነው

ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ይህ በፌስ ቡክ፦”shocking photo ”(አስደንጋጭ ፎቶ” ) በሚል ርዕስ ስር የተለቀቀው የአቶ መለስ ዜናዊ አያት የባሻ አስረስ ፎቶ፤ ባሻ አስረስ  ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ሹመት በተቀበሉበት ቀን የተነሱት ነው ።

በፎቶው ላይ የአቶ መለስ አያት ባሻ አስረስ ተሰማ፤ ሹመት በሰጧቸው የጣሊያን የጦር አዛዥ ጎን ቆመውና በተከታዮቻቸው ታጅበው ይታያሉ።

አቶ ገብረመድህን አርአያን ጨምሮ የአቶ መለስ ዜናዊን  ቤተሰቦች በቅርብ የሚያውቋቸው ሁሉ፤ አባታቸው አስረስ ዜናዊም ሆኑ አያታቸው ባሻ አስረስ ተሰማ የጣሊያን ባንዳ በመሆናቸው ሳቢያ በአካባቢው ህብረተሰብ ይገለሉ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም።

በዚሁ የቤተሰብ  ታሪክ ምክንያት አቶ መለስም ሆኑ ታላቅ ወንድሞቻቸው በሙሉ አድዋ ውስጥ የትምርት ቤት ጓደኛ እንኳ እንዳልነበራቸው ያስታወሱት እነዚህ ወገኖች፤ አቶ መለስ አሁን  በሥልጣን ላይ እያሳዩት ያለው  ባህርይ ከአስተዳደጋቸውና ከሁዋላ ታሪካቸው ጋር በቀጥታ የተገናኘ እንደሆነ በ እርግጠኝነት ይናገራሉ።

አቶ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ  ታሪክ ጥላቻ እንዳላቸው የተለያዩ ዲፕሎማቶች ሳይቀር የሚናገሩት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሀት የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ ለማስጻፍ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡ ይታወቃል።  አዲሱ ታሪክ የኢትዮጵያን የ100 አመት እድሜ ለማረጋገጥ የሚጻፍ ይሁን አይሁን እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጅ አዲስ ታሪክ የመጻፉ ስራ በህወሀት የደህንነት ሰራተኛ በነበረው እና ብዙ ሰብአዊ ግፎችን ፈጽሞአል በሚባለው በአቶ በስራት አማረ አጼ ሚኒሊክን የማንቋሸሽ ስራ ተጀምሯል።

አቶ መለስ ዜናዊም ግለ ታሪካቸውን ማስጻፋቸው ይታወሳል።