የአትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ምርጫ አልተሳካም ሲሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያነጋገርናቸው ኢትዮጳያዊያን ሙስሊሞች ተናገሩ

መስከረም ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንደተደረገ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን የዘገቡ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ግን ምርጫው አልተሳካም ሲሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያነጋገርናቸው ኢትዮጳያዊያን ሙስሊሞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምርጫው በተጀመረ በጥቂት ሰኣታት ውስጥ ለምርጫው ከተመዘገበው 7 ሚሊዮን ህዝበ ሙስሊም ውስጥ 95 ከመቶው ድምጹን እንደሰጠ ሲናገሩ፤ ከአዲስ አበባ ያነጋገርናቸው ሙስሊሞች ግን፤ በምርጫው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩም አልተሳተፉም፤ እንዲያውም፤ በየቀበሌው የተገኙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለቴሌቪዥን ዜና ያመች ዘንድ የየቀበሌዎቹ መራጮች ወደወረዳ እንዲሰበሰቡ ተደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በኢሉ አባቦራ፤ በጅማ፤ በሰበታ፤ በሱሉልታ፤ በአርሲ፤ በባሌ፤ በወልቂጤ፤ በደሰሴ በከሚሴ፤ በከፋ፤ እንዲሁም በሌሎች ከተሞችም ምርጫው በስኬት እንዳልተጠናቀቀና፤ ባንዳንድ ስፍራዎች ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞም እንደነበር ታውቋል።

ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም፤ ባንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች፤ ሰው እየተንጠባጠበ ሲመጣ፤ የተመረጡ ሰዎች ስም ዝርዝር የያዙ ሰዎች፤ ተወካዮች ተመርጠዋል፤ ወደቤት ተመለሱ በማለት መራጮቹን እንዳስመለሷቸው ታውቋል።

ከአዲስ አበባ ያነጋገርነው ኢትዮጵያዊ እንደገለጸው፤ አንድ የሬድዮ ፋና ጋዜጠኛ ከአዲስ ከተማ ከሚገኝ ምርጫ ጣቢያ ባስተላለፈው ቀጥታ ዘገባ፤ ብዙ መራጮች እንዳልነበሩና፤ የመጡትም ዘግይተው እየተንጠባጠቡ እንደመጡ አምኗል።

የመጅሊሱን ምርጫ ሕገጋዊ አይደለም ብለው የሚከራከሩ ሙስሊሞች ለምርጫው ከተገኙት ውሱን ቁጥር ያላቸው መራጮች ውስጥ፤ ግማሾቹ ከቀበሌ ቤት ትወጣላችሁ፤ የቦኖ ውሀ ይቋረጥባችሁዋል፤ በግብር እናሰቃያችኋለን፤ የኤድስ መድሀኒት አንሰጣችሁም፤ በሚል ማስፈራሪያ እንዲመርጡ እንደተገደዱ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የመጅሊሱ ምርጫ ሁኔታ እስካሁን ወደልማት እንዳንገባ አግዶን ነበር፤ ከምርጫ በሁዋላ ግን ወደልማታችን እንመለሳለን ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ የሙስሊሙ ተቃውሞ አስተባበሪዎች ግን ትግላችን ከበፊቱ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

በሌላ ዜና፤

ባለፈው አርብ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ወደ ቢጫ ካርድ ያደገው ተቃውሞ፤ ወደሰሜን አሜሪካም የተዛመተ ሲሆን፤ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ አያሌ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፤ ባለፈው ቅዳሜ፤ መስከረም 26 ቀን ከሰዓት በሁዋላ ስብሰባ አድርገው መንግስት በሀይማኖታቸው ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል።

በሩዝቬልት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ላይ ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝና ምሁር ጃዋር ሙሀመድ ባቀረበው ሰፊ ንግግር፤ የሙስሊሙን ትግል መንስኤና ባለፉት 11 ወራት ያለፈበትን ደረጃዎች ተንትኗል።

የኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው አቶ ጃዋር መሀመድ፤ የሙስሊሙ ሕ/ሰብ ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በንጽጽር ከበፊቶቹ ስርአቶች በተሻለ ከኢህአዴግ ጋር የመከባበር ግንኙነት ቢኖረውም፤ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን፤ በሶስት አብይ ምክንያቶች የተነሳ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ በመግባቱ፤ ከሙስሊሙ ሕ/ሰብ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል ብሏል።

አንደኛ፤ አምባገነን ስርቶች ህዝብ ነጻና እነሱ የማይቆጣጠሩት የሀይማኖት አመራርና ተቋም ስለሚያሰጋቸው፤ ሁለተኛ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ፤ የተጨቆኑና የተበደሉ ብሄሮች ብሎ ተነስቶ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከነዚህ የተጨቆኑ ብሄሮች ያገኘው ድጋፍ እየተመናመነ ስለሄደ፤ የተመናመነውን ድጋፍ በሀይማኖታዎ ፖለቲካዊ ድጋፍ ለመተካት በመፈለጉ፤ ሶስተኛም ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የውጪውን ድጋፍ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት የተነሳ በሙስሊሙ ጉዳይ ገብቶ ለመፈትፈት በመሞከሩ፤ ከሙስሊሙ ጋር ግጭት ውስት ገብቷል ብሏል።

መንግስት በተለያየ ሰዓት በሚያወጣቸው መግለጫዎች የሙስሊሙን ጥያቄ መጥፎ መልክ በመስጠት በክርስቲያኑ ሕ/ሰብ ላይ ስጋትን ለመፍጠር ቢጥርም፤ የሙስሊሙ አመራሮች ግን ትግሉን ሕገመንገስታዊ እንዲሆን በማድረግ፤ አርብ ወይም ጁምአ፤ እንዲሁም በመስጊድ ብቻ እንዲወሰን በማድረግ፤ የመንግስትን ትንኮሳ ችሎ በማለፍና፤ “የምንሞትለት አላማ አለን፤ የምንገድልበት አላማ ግን የለንም በማለት፤” እስካሁን ያለውን ሂደት በድል ተወጥተዋል ብሎ ለሙስሊሞቹ አመራሮችና ለተቃውሟቸው ያለውን አድናቆት ገልጿል።

እስካሁን የመጣንበት የትግል መንገድ ወደፊትም ተጠብቆ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰበው ጁዋር መሀመድ፤ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የአመራር ሳይሆን የድጋፍ ሰጪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ፤ ጸሎት በማድረግ፤ እንዲሁም የቁሳዊና የሞራል ድጋፍ በመስጠት እርዳታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧል።

በዚህ ሕዝበ ሙስሊሙ የአገር ቤቶቹን ሙስሊሞች አርአያነት በመከተል ቢጫ ወረቀቶችን ይዞ በተገኘበት ስብሰባ ላይ፤ ከግማሽ በላይ ተሰብሳቢዎች ሴቶችና ህጻናት ሲሆኑ፤ በጥያቄና መልስ ክ/ጊዜም ሴቶች ተሳትፎ አሳይተዋል።

ምርጫችን በመስጊዳችን፤ መንገስት በሀይማኖታችን ጣልቃ መግባት ያቁም፤ አላሁዋክበር የሚሉ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን፤ የተለያዮ ግጥሞችም ቀርበዋል።

በስብሰባው ላይ አብራር አብዶ የሚተውንበት “ጀዝኣ” የተሰኘ ፊልም የታየ ሲሆን፤ በመጨረሻም ሰላት ተደርጎና፤ ሙስሊሙ ሕ/ሰብ በአገር ቤት ለሚደረገው ትግል አጋርነቱን ላማሳየት ቃል ኪዳኑን አድሶ የስብሰባው ፍጻሜ ሆኗል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide