“የአባይ ግድብን በራስ አቅም እንገነባለን” የሚለው ቅስቀሳ ጥያቄ ውስጥ ገባ

መጋቢት ፳ (ሃያ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፉት ስድስት ዓመታት ለግድቡ የቦንድ መዋጮ 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ የቦንድ አሰባሳቢ ግብረሃይሉ ባስታወቀው መሰረት መሰብሰብ የተቻለው 9 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲያዋጣ የተገደደውም የመንግሥት ሠራተኛው ነው።
ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩት የመንግሥት ሠራተኞች በየመ/ቤታቸው ሳይወዱ በግድ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ 5 ቢሊየን ብር በላይ አዋጥተዋል፡፡ እስካሁን ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ የባለሃብቱ ጠቅላላ ድርሻ ከ2 ቢሊየን ብር የበለጠ አለመሆኑ ባለሃብቶች ለግንባታው የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የሚያመልክት ነው ተብሏል፡፡ በውጪ ሀገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ይለግሳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በ6 ዓመታት ውስጥ ቦንድ የገዛው መጠን 800 ሚሊየን ብር ገደማ ነው፣ ይህም በውጪ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊን ብዛት አንጻር መዋጮው እዚህ ግባ የሚባል ዓይነት አለመሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች አስረድተዋል፡፡
በባለሃብቱም በኩል በተለይ የቦንድ ሰርተፊኬቱ ለባንክ ብድር ማዋል የማይቻል መሆኑ ከመረጋገጡ ጋር ተያይዞ ለግድቡ ከፍተኛ ገንዘብ ለማዋጣት በበርካታ ባለሃብቶች ዘንድ ፍላጎት አለመታየቱ፣ ቃል የገቡትም ወገኖች የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ገንዘቡን ለመልቀቅ ፍቃደኝነት ማጣታቸው በገዢው ፓርቲ በኩል የተያዘውን ዕቅድ አኮላሽቷል፡፡
ለግድቡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰብ የአገዛዙ ከፍተኛ ካድሬዎች የተንቀሳቀሱ ቢሆንም የገንዘብ አሰባሰቡ የአሜሪካ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የተካሄደ ባለመሆኑ ሊታገድ ችሏል፡፡
ኢህአዴግ የግድቡን ግንባታ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ፣ ይደግፉኛል ከሚላቸው ወገኖች በስተቀር ሌሎችን ወገኖች ለማሳተፍ አለመፈለጉና ከኢትዮጵያውያን የሚቀርብለትን ቅድመ ሁኔታ ለመመለስ ባለመፈለጉ ምክንያት ባለፉት ስድስት ዓመታት ለፕሮጀክቱ ከሚፈለገው 80 ቢሊየን ብር ገንዘብ ውስጥ ከኢትዮጵያ የተሰበሰበው አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በቂ ገንዘብ መሰብሰብ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ አገዛዙ ከአቅሙ በላይ በሆነ መንገድ ለመደጎም በመገደዱ፣ እንደቴሌ፣ አየር መንገድ ያሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ገቢ ሙሉ በሙሉ ለግድቡ ሥራ እየዋለ መሆኑም ታውቋል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት የፕሮጀክቱ ወጪ 80 ቢሊየን ብር የተባለው ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ከብር መውደቅ ጋር ተያይዞ ወጪው ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ ስድስት ዓመት ተጉዞ 50 በመቶ መጠናቀቁ እየተነገረ ነው፡፡ ቦታው ድረስ የተገኙና የታዘቡ ወገኖች ግን የግንባታው እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ይገልጻሉ።