የአርበኞች ግንቦት7 አባላት አንድ ኮማንደርን ጨምሮ በርካታ ወታደሮችን መግደላቸውን ገለጹ

ሰኔ ፲፪( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ድርጅቱ ለኢሳት በለካው መረጃ የአርበኞች ግንቦት7 ልዩ ኮማንዶ በእብናት ከተማ ወታደራዊ ጊዚያዊ ጣቢያ ላይ ሰፍሮ በሚገኙ ወታደሮች ላይ በወሰዱት ጥቃት የጦሩ አዛዥ የሆነውን ኮማንደር አወቀን ጨምሮ በርካታ ወታደሮችን መግደላቸውን አስታውቀዋል።
ኮማንደሩ በከፍተኛ ወታደራዊ አጀብ ወታደራዊ አመራሮች፣ የክልል ባለስልጣናት፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት አርማጭሆ ላይ መቀበሩን የገለጸው ድርጅቱ፣ አዛዡ አስቀድሞ የአርበኞች ግንቦት7 አባላትን እንደሚደመስሳቸው ለአለቆቹ ቃል ገብቶ ነበር ብሎአል።
ንቅናቄው በራሱ በኩል ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበትና ታጋዮቹ በሰላም ወደ መጡበት መመለሱን ገልጿል። ጥቃቱ በሌሊት በመካሄዱ የሟቾቹን ቁጥር በትክክል ለማወቅ እንዳልተቻለ ድርጅቱ ገልጾ፣ በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረታቦር፣አዲስ ዘመን፣እብናት፣ወረታ፣ ልማትበርና ወደ ባህርዳር መግቢያ ቦታዎች ድረስ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሰራዊት ተሰማርቶ በመንገደኞች እና በተሽከርካሪዎች ተጭነው በሚሄዱ መንገደኞች ላይ ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማድረግ ላይ መሆኑም አክሎ ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ አርበኞች ግንቦት 7 አገኘሁት ባለው ድል ዙሪያ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠም። አርበኞች ግንቦት7 በተደጋጋሚ ለሚያወጣቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች ገዢው ፓርቲ መልስ ሰጥቶ አያውቅም። የአካባቢውን ሰዎች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።