የአምባሳደሮች ወደሀገር የመመለስ ጉዳይ አነጋጋሪ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 10/2009) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በዲፕሎማቶቹ ላይ በጀመረው ብወዛ ከእነ አምባሳደር ግርማ ብሩ በተጨማሪ በካናዳ፣ሲውዲን፣ሱዳን፣ደቡብአፍሪካ፣ኳታር፣ዩናይትድ አረብ ኢምሬትና ሩዋንዳ የሚገኙ አምባሳደሮችን በማንሳት በአዳዲስ ተሿሚዎች መተካቱን አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩ በብአዴኑ ካሳ ተክለብርሃን መተካታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በቻይና ቤጂንግ የሚገኙት አቶ ስዩም መስፍንም በሌላው የሕወሃት አባል በአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ መተካታቸውን አስታውቋል።
አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የተጠሩት አምባሳደሮች ወደሀገር የመመለስ ጉዳይ የታወቀ ነገር የለም።
አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ሌሎች አምስት አምባሳደሮች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ጥሪ መቅረቡ የታወቀው አስቀድሞ ነበረ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደረገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ በካናዳ ፣ በሲውዲን ፣በሱዳን ፣በደቡብአፍሪካ ፣በኳታር፣በዩናይትድ አረብ ኢምሬትና ሩዋንዳ ተመድበው የነበሩትን አምባሳደሮች በማንሳት በአዳዲስ ተሿሚዎች መተካቱን አስታወቋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩ በብአዴኑ ካሳ ተክለብርሃን መተካታቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያረጋገጠ ሲሆን በቻይና ቤጂንግ የሚገኙት አቶ ስዩም መስፍንም በሌላው የሕወሃት አባል በአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ መተካታቸውን ገልጿል።
በቻይና ጉዋንጉዞ የሚገኙት ካውንስል ጄኔራል አቶ ገብረሚካኤል ገብረጻድቅ በስፍራቸው ቀጥለዋል።
በቻይና በአምባሳደርነትም በካውንስል ጄኔራልነትም በቋሚነት የቀጠሉት የሕወሃት አባል ብቻ ስለመሆናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠው ማብራሪያ የለም።
በሱዳን ለረዥም ጊዜያት ያገለገሉት የሕወሃቱ አባል አቶ አባዲ ዘሙ በሌላው የሕወሃት አባል አቶ ሙሉጌታ ዘውዴ ተተክተዋል።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ ተነስተው በምትካቸው የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ወይዘሮ አስቴር ማሞ ሲተኳቸው የስውዲኗ አምባሳደር ወይዘሮ ወይንሸት ታደሰ ደግሞ በምርጫ ቦርዱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ተተክተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በደቡብ አፍሪካ ሲሾሙ አቶ ተበጀ በርሄ ወደ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ተልከዋል።
በኳታር የሚገኙት አቶ ምስጋኑ አርጋ በወይዘሮ መታሰቢያ ታደሰ ሲተኩ፣ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ አሊ ሱሌይማን በፈረንሳይ ፓሪስ ተሰይመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ ወደ ኢንዶኔዢያ ጃካርታ ሲላኩ የቀድሞ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ በቤልጂየም ብራስልስ መመደባቸው ታውቋል።
ከተጠሩትና ምትካቸው ሰዎች ከተሾሙባቸው አምባሳደሮች ምን ያህሉ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ የታወቀ ነገር የለም።
በዩ ኤስ አሜሪካ የኢትዮጵያ ኣአምባሳደር ሆነው ላለፉት ረጅም አመታት ያገለገሉት አቶ ግርማ ብሩ የሙስና ማለትም ሌቦቹን የማሰሩ እርምጃ እስኪቆም ወደ ሀገር ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ ወስጥ አዋቂ ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።