የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት እየፈጸመ ነው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲያቆም ጠየቁ

ኢሳት (የካቲት 10 ፥ 2009)

አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ  መብት ጥሰቶች ዕርምጃ እንድትወስድ ለሃገሪቱ ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብን ያቀረቡ የምክር ቤት አባላት፣ የኢትዮጵያ መንግስት እየፈጸመ ነው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲያቆም ጠየቁ።

በዚህ በአሜሪካ የኒውጀርሲና የኮሎራዶ ግዛት የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባላት የሆኑት ሚስተር ክሪስ ስሚዝ እና ማይክ ኮፍማን ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ተቃዋሚ አካላትን ለማጥፋት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫን ያወጡት ሁለቱ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ አካላት መንግስት እየፈጸመ ያለውን ዕርምጃ እንዲያቆም ቢጠይቁም ድርጊቱ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱ ገልጸዋል።

በአሜሪካ ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች የሚከታተል ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት ክሪስ ስሚዝ ባለፈው አመት በብራዚል በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር በሃገሪቱ ያለውን ግድያና አፈና ለአለም ለማሳወቅ አስተዋጽዖ ያደረገው አትሌት ፈይሳ ለሊሳ የማይረሳ ተግባር መፈጸሙን አውስተዋል።

ይኸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችላ ሊባል የማይችል መሆኑን የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ በመሄድ ላይ መሆናቸውን አክለው አስታውቀዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል ማይክ ኮፍማን በበኩላቸው የሃገራቸው መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት እና የሃገሪቱ ህገመንግስት ድንጋጌዎች ጥሰቶችን በቅርቡ በመከታተል ላይ መሆኑን አውስተዋል።

ይኸው ሃሳብ በአብዛኛው የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ በምክር ቤቱ ለውሳኔ እንዲቀርብ ጥረትን እያደረጉ ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ዘመቻቸው አሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች የምክር ቤት አባላቱ የከፈቱትን ዘመቻ በመደገፍ ከወራት በፊት የድጋፍ ፊርማቸውን ለአሜሪካ መንግስት አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

በገዢው የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው ሲና ጅምጅሞ፣ ቴዎድሮስ ትርፌ፣ እና ጉያ አባጉያ የተባሉ ግለሰቦች በዚሁ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን የደረሰባቸውን ስቃይ በዝርዝር አስፍረዋል።

ለአንድ አመት ያህል በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ሰዎች ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ በማቆም ለተቃውሞ ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እንዲሰጥ ስታሳስብ ቆይታለች።

በሃገሪቱ በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውንን የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎም አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያን ሰጥታ ትገኛለች።