የታይላንድ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ የተጓጓዘው የአውራሪስ ቀንድ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላትን ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆናቸውን ገለጹ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2009)

የታይላንድ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ከተጓጓዘውና በሃገሪቱ አለም አቀፍ አውሮፓላን ማረፊያ ማክሰኞ ከተያዘው 21 የአውራሪስ ቀንድ ዝውውር ጋር የተገናኙ አካላት ለማወቅ ምርመራ መጀመራቸውን አስታወቁ።

አምስት ሚሊዮን ዶላር (ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ) ግምት ያለው ይኸው የአውራሪስ ቀንድ በአየር ማረፊያው በጥርጣሬ በተካሄደ ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን ቢቢሲ ዘግቧል። መነሻውን ከኢትዮጵያ ያደረገው ሻንጣ ለመረከብ በአየር ማረፊያው ከቬይትናምና ከካምቦዲያ የተጓዙ ሁለት የታይላንድ ሴቶች ሻንጣው ለፍተሻ መወሰዱን ባስተዋሉ ጊዜ ከስፍራው መሰወራቸው የታይላንድ ፖሊስ አስታውቋል።

ይሁንና ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በሻንጣ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ስር ከዋለው የአውራሪስ ቀንድ ዝውውር ጋር የተገናኙ አካላትን ለማወቅ የሃገሪቱ የጸጥታ አባላት ምርመራ መጀመራቸውን ይፋ አድርገዋል።

ከቤትናምና ካምቦዲያ ሻንጣውን ለመረከብ በስፍራው የነበሩትን ሁለት ታይላንዳዊያን ሰዎችን አድኖ ለመያዝም ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የግለሰቦቹ መያዝ ለምርመራው እገዛ እንደሚያደርግ የጸጥታ አባላት ተናግረዋል።

የታይላንድ ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ መጀመሩን ቢገልጹም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውራሪስ ቀንዱ እንዴትና በማን ይጓጓዝ እንደነበር እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

የዱር አራዊት መብት ተሟጋች አካላት በበኩላቸው ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የአውራሪስ ቀንድ በአንድ ጊዜ በቁጥጥር ስር መዋሉ አስደንጋጭ መሆኑን ገልጸዋል።

የአውራሪስ ቁጥር በአለማችን በመመናመን ላይ መሆኑን ተከትሎ የአውራሪስ ግድያና የቀንዱ ዝውውር በአለም አቀፍ ደረጃ ህገወጥ ተደርጎ ተደንግጓል።

በአሁኑ ወቅት 29ሺ አካባቢ ብቻ አውራሪሶች በአለማችን ሲሆኑ ቀንዳቸውንም በተለይ በኤዥያ ለተለያዩ ባህላዊ ህክምናዎች እንደሚውል የአለም አቀፍ አውራሪስ ፋውንዴሽን መረጃ ያመለክታል።

በቅርቡ መነሻውን በአዲስ አበባ ያደረገና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 2 ኪሎግራም ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በተመሳሳይ መልኩ በካምቦዲያ በተመሳሳይ መልኩ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።