የታሰሩ ወጣቶች ቁጥር መንግስት ይፋ ካደረገው እንደሚበልጥ ከእስር ቤት ያመለጠ ወጣት አጋለጠ

ጥር 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፉት አራት ወራት የኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች የህዝብ አመጽ ለማስነሳት ይቀሰቀሳሉ ብለው የሰሩዋቸው ወጣቶች ቁጥር መንግስት ይፋ ካደረገው አሀዝ በእጅጉ እንደሚበልጥ አንድ ከእስር ቤት ያመለጠ ወጣት አጋለጠ

ለደህንነቱ ሲባል ስሙን ለመግለጥ የማንፈልገው ወጣት ባለፈው ሳምንት ታስሮበት ከነበረው የታጠቅ እስር ቤት አምልጦ እንዲወጣ በተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ነበር።

ወጣቱ ከእስር ቤት አምልጦ እንደወጣ ወዲያውኑ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በአለፉት 4 ወራት አመጽ ለማስነሳት ስትቀሰቅሱ ነበር ተብለው እንደርሱ የተያዙና በታጠቅ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ እስርኞች አለ።

የዛሬ አራት ወር ገደማ ፒያሳ አካባቢ ሲቪል የለበሱ የደህንነት አባላት ትፈለገላህ ብለው እንደወሰዱት የገለጠው ወጣት፣ በምሽት አይናቸው እየተጨፈነ ከበርካታ ወጣቶች ጋር በአንድ ትልቅ የጭነት መኪና መወሰዳቸውን ገልጧል።

ማታውኑ እያንከባለሉ ሲገርፉዋቸው ካመሹ በሁዋላ ከ100 በላይ የሚሆኑትን ወደ አንድ ክፍል ሌሎችንም እንዲሁ ወደ ሌላ ክፍል እንደወሰዱዋቸው ተናግሯል።

ውሀ ውስጥ ይደፍቁናል፣ ይገርፉናል፣ አድካሚ ስፖርት ያሰሩናል፣ ሲደክመን ደግሞ ይረግጡናል የሚለው ወጣት፣ እስከ ዛሬ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን  የመገናኛ ብዙሀንም ስለ እነርሱ እንደማያወቁ ተናግሯል።

በምርመራው ወቅት የተለያዩ ስሞችን ይጠሩልን ነበር፤ የግንቦት7 አባል ነህ? ከኢሳት ጋር ትገናኛለህ? ከአንዱአለም ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድ ነው? እከሌ ከሚባለው ጋዜጠኛ ጋርስ አልተገናኘህም? ምን ተልእኮ ሰጠህ? የሚሉ ጥያቄዎች ለእስረኞች ይቀርብላቸው እንደነበር የገለጠው ወጣት፣ እስረኞቹ አላውቅም የሚል መልስ ከሰጡ በጥፊና በቦክስ ይመታሉ ብሎአል።

በታጠቅ ውስጥ ያለውን የእስረኞች ቁጥርና የሚደርሰውን ስቃይ ፈጽሞ ለመግለጥ አይቻልም የሚለው ወጣት፣ በየጊዜው የሚሞቱ እስረኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም ብሎአል።

በአመጽ መቀስቀስ የታሰሩት ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይቀላቀሉ መደረጋቸውንም ወጣቱ ገልጧል።

በአሁኑ ጊዜ ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለብኝ ገና አልወሰንኩም፣ የጀመርኩትን የነጻነት ትግል ከዳር ለማድረስ ጥሩው አማራጭ የትኛው እንደሆነ እያሰብኩ ነው፤ አሁን በቅድሚያ ራሴን በአስተማማኝ ሁኔታ የምደብቅበትን መንገድ መተለም አለብኝ፤ ከያዙኝ ያልቅልኛል ብሎአል።

ሂማውን ራይትስ ወችን ጨምሮ ሌሎች አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የአረቡ አለም ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ 400 ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበራት መታሰራቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ ፍርድ ቤት እና መገናኛ ብዙሀን ያላወቋቸው በተለያዩ እስር ቤቶች የሚማቅቁ ወገኖች ቁጥር ከዚህ አሃዝ በብዙ እጅ እንደሚልቅ የሚደርሰን መረጃ ያመለክታል።

ኢሳት ከሶስት ወራት በፊት በአማራ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ወጣቶች መኖራቸውን ዘግቦ ነበር። አንደኛው ወጣት በቅርቡ መፈታቱን ፍኖተ ነጻነት የእሰረኛውን ቃለምልልስ በመያዝ መዘገቡ ይታወሳል።

በታጠቅ እስር ቤት ውስጥ የሚታጎሩ እስረኞች ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማያወቁ በግቢው ውስጥ ታስረው ለረጅም ጊዜ የቆዩ እስረኞች ይናገራሉ። ኢሳት በታጠቅ እስር ቤት ውስጥ ስለሚካሄደው ግፍ በቅርቡ አንድ ዘገባ ያቀርባል።