የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በሶማሊላንድ ወታደራዊ ጣቢያ ለማቋቋም ስምምነት መድረሷ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 6 ፥ 2009)

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው የሶማሊላንድ ወታደራዊ ጣቢያ ለማቋቋም ስምምነት መድረሷ ተገለጸ።

የተባበሩት ኤሜሬት የወሰደችው ይኸው እርምጃ በጎረቤት ሃገራት ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱን ቢቢሲ የፖለቲካ ተንታኞችን ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል።

የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት አህመድ ሞሃመድ ሱላኒዬ የሶማሊላንድ ሃገሪቱ የወሰደችው ዕርምጃ ስራን ለመፍጠር ጠቀሜታ እንዳለው ለፓርላማ አባላት መግለጻቸው ታውቋል።

144 የሚሆኑ የፓርላማ አባላት ወታደራዊ ጣቢያው እንዲቋቋም ድጋፍን የሰጡ ሲሆን፣ ዘጠኝ ተቃውሞ ያቀረቡ የፓርላማ አባላት ደግሞ በጸጥታ ሃይሎች እንዲወጡ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ተጨማሪ ሁለት አባላት ድምፅ ከመስጠት የተቆጠቡ መሆኑንና ሁለት አባላት ደግሞ ተቃውሞ ማስመዝገባቸው ተመልክቷል። ባለፈው አመት አንድ የተባባሩት አርብ ኤሜሬት ኩባንያ የበርበራ ወደብን ለማስፋፋት እና ከሶማሊላንድ ጋር በጋራ ለመጠቀም የ442 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ከሶማሊላንድ ጋር አመታትን የቆየ ድርድር ስታካሄድ ብትቆይም በሁለቱ መካከል ስምምነት ሳይደርስ መቅረቱን ለምረዳት ተችሏል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በአፍሪካ ቀንድ እያደረገች ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጎረቤት ሃገራት መካከል ጥርጣሬ ማሳደሩን የፖለቲካ ታዛቢዎች በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል። ሃገሪቱ በየመን እያካሄደች ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ለማገዝ ተመሳሳይ ጣቢያን በኤርትራ እንዳቋቋመች የዜና ወታሩ አመልክቷል።

ሳውዲ አረቢያ በየመን አማጺያን ላይ እያካሄደች ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ በመደገፍ ላይ የምትገኘው የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ይህንኑ ዘመቻዋ ለማጠናከር አማራጮችን እየተጠቀመች እንደሆነ ይነገራል።

ሳውዲ አረቢያ በበኩሏ በየመን እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ለማጠናከር በኤደን ባህረ ሰላጤ የጦር መርከቦችን አሰማርታ የምትገኝ ሲሆን፣ በየመን ከሁለት አመት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን ድረስ ከ10ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን  ተመድ ይገልጻል።