የተቅማጥ (አተት በሽታ) በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል

ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአገሪቱ ከሚታየው ድርቅና የንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ከፍተኛ ስጋር ፈጥሯል። በአዲስ አበባ የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ ነው ቢባልም፣ በዚህ ሳምንት ብቻ 25 በሽተኞች ህክምና ማግኘታቸውን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአማራ ክልል በ21 ወረዳዎች ፣ በትግራይ 5 ወረዳዎች ፣ በኦሮሚያ 16 ወረዳዎች ፣ በደቡብ 12 ወረዳዎች ፣ በኢትዮጵያ ሶማሊ 12 ወረዳዎችና በአፋር 3 ወረዳዎች በያዝነው ሳምንት በሽታው በስፋት ተሰራጭቷል። በሽታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ መከሰቱ ነው። በሶማሊ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በበሽታው ህይወታቸው ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።
በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ ነዋሪዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት እንስሶቻቸው በማለቃቸው መኖሪያ ቀያቸውን በመተው እየፈለሱ መሆኑን የረድኤት ድርጅቶች አስታውቀዋል። አርብቶ አደሮቹ በምግብ እና ውሃ እጥረት ክፉኛ በመጎዳታቸው ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ መጠለያ ካንፖች አመርተዋል።
የ82 ዓመቱ አዛውንት አቶ አብዱከሪም ”አሁን አካባቢያችን በከፍተኛ ድርቅ ተጠቷዋል። እኔ በእድሜዬ እንደዚህ ዓይነት ርሃብ አይቼ አላውቅም’ ብለዋል። የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳሬክተር የሆኑት ቻርሊ ማሶን በበኩላቸው ”አብዛሃኞቹ የቤት እንሳስቶቻቸው ሞተውባቸዋል። የቀሩዋቸውን እንስሣት ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ ያላቸውን ጥቂት ገንዘብ እያፈሰሱ ነው። እነዚህ ሁሉ ሁለመናቸውን ያጡ ዜጎች በመንግስት አስፈላጊውን የምግብ እና የውሃ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲሉ ተማጽኖዋቸውን አሰምተዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ በድርቁ ምክንያት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋቸው የሚተመን የቤት እንስሳት አልቀዋል። በአሁኑ ወቅት ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ሲሆኑ፣ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ሲል ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል። በምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች እርዳታ የሚውል በዚህ ዓመት ብቻ 948 ሚሊዮን ዶላር ቢያስፈልግም እስካሁን ግን የተገኘው 23.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳሬክተር የሆኑት ኤድዋርድ ብራውን በበኩላቸው ”ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በመንግስት እና እረድኤት ድርጅቶች የተሰጠው ምላሽ ሰፊ ክፍተት አለው። በርሃብ የተጎዱ ዜጎችን ሕይወት በአፋጣኝ ለመታደግ ከተመድ እና የአሜሪካ መንግስት አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልጋል።” ብለዋል።
በአገር ውስጥ ብቻ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ 400 ሽህ ኢትዮጵያዊያን የሚውሉ 222 ጊዜያዊ መጠለያዎች በዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ተዘጋጅተዋል። በመጠለያዎቹ ውስጥ ከተጠለሉት መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በቂ ምግብ የማያገኙ ሲሆን 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ20 ደቂቃ ጉዞ በኋላ በእግር ተጉዘው ውሃ ያገኛሉ።
አንድ ከፍተኛ የረድኤት ሰራተኛ በአካባቢው የተፈጠረውን ረሃብ ሲገልጸው፣ ”ያላቸውን ጥሪቶች በማውጣት ሕይወታቸውን ለማትረፍ የቻሉትን አድርገዋል። አሁን ግን ምንም ዓይነት ነገር የላቸውም” ሲል የሰብዓዊ ቀውሱ የከፋ መሆኑን አስረድቷል። በምስራቃዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ከዶሎ አዶ ከተማ 70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኙት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ650 በላይ ቤተሰቦች ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳልደረሳቸውም አክሎ ገልጿል።
በምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የቤት እንሳሳት ከመሞታቸው በተጨማሪ ያሉትም ቆዳቸው በላያቸው ላይ የተጣበቀ የመሞቻ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለምአቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሰብዓዊ ቀውሱ በሰው እና በቤት እንሳስት ሕይወት ላይ የከፋ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት በአፋጣኝ ሕይወት የማዳን ሥራዎችን ላይ ሊሳተፉ ይገባል ሲል ኢርኒ የዜና ወኪል ዘግቧል።