የተምች ወረርሽን በ6 የኢትዮጵያ ክልሎች ተከሰተ

 

ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ የተረጂዎች ቁትር ከ5.6 ሚሊዮን ወደ 7.8 ሚሊዮን በተሻገረበት ወቅት በ6 የሀገሪቱ ክልሎች የተምች ወረርሽን መከሰቱ ተገለፀ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው በ35 ዞን 233 ወረዳዎች ችግሩ ተከስቷል። 

የተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ ዕርዳት ማስተባበሪያ ቢሮ ወረርሽኙን በቅድሚያ የተከሰተው በደቡብ ክልል ሻላ ዞን የኪ ወረዳ ቢሆንም አሁን በ6 ክልሎች ተጨማሪ 232 ወረዳዎችን አጥቅቷል። ወረዳዎቹ የችግሩ ተጠቂ የሆኑት ካለፈው የካቲት ወዲህ እየተስፋፋ በቀጠለው ወረርሽኝ መሆኑንም ተመልክቷል።

በ233ቱ ወረዳዎች ተምቹ ባደረስው ጉዳት 145ሺህ ሔክታር ላይ የተዘራ የበቆሎ ሠብል ተጠቅቷል።

የአማራ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሚያ እንዲሁም የትግራይና ደቡብ ክልል በተምች ወረርሽኙ የተጎዱ ክልሎች መሆናቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብዓዊ ዕርዳታ ማሥተባበሪያ ኮሚሽን ገልፃል። በአጠቃላይ በተከሠተው ድርቅ ተጨማሪ አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግም ጥሪ አቅርቧል።