የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የመንግስት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ውድቅ አደረጉት

ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)

በህወሃት አገዛዝ የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት በቅርቡ አዲስ አበባን የጎበኙት የተባባሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ውድቅ አደረጉት።

ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አልሁሴን በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብቻ ከ26 ሺ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም የተፈጸመው ግድያ በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንደሌለ ያሳያል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ግን ከእርሳቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ኮሚሽነሩ ተቀብለውታል። እውቅናም ሰጥተውታል በማለት የሃሰት መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል።

ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አልሁሴን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች አመጽ የተነሳባቸው አካባቢዎች እንዲጎበኙ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያቀረቡት ጥያቄ አሁንም ተቀባይነት አላገኘም።