የተለጣፊው የኦብኮ ሊቀመንበር በፖሊሶችና በተበዳዮች ርብርብ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የተለጣፊው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ (ኦብኮ) ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፤ በትናንትናው ዕለት በሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ በፖሊሶችና በተበዳዮች ርብርብ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

 አስር አለቃ ቶሎሳ ተስፋዬ፤መንግስት  በምርጫ 97 ወቅት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ በመውጣት ወደ 40 የሚጠጉ የፓርማ መቀመጫዎችን ያገኘውንና  በዶክተር መረራ ጉዲና የሚመራውን  ኦብኮ ለማፍረስ ሢንቀሳቀስ፤ በዋነኝነት የተጠቀመባቸው  የፓርቲው አባል የነበሩ ግለሰብ ናቸው።

 በወቅቱ በፖሊሶች ታጅበውና ሽጉጥ ይዘው ወደ ኦብኮ ጽህፈት ቤት በመግባት፤ ሠራተኞቹን አግተው የጽህፈት ቤቱን ዶክመንቶችና ማህተም ጭምር  ይዘው ከመውጣታቸውም በላይ፤ ተለጣፊ ኦብኮ እስከማቋቋም መድረሳቸው አይዘነጋም።

 ራሳቸውን የኢህአዴግ ወዶ ገብ አገልጋይ በማድረግ እናት ድርጅታቸውን እስከማፍረስ የደረሱት አስር አለቃ ቶሎሳ፤    ቀደም ሲል ጀምሮ የተመሰረቱባቸውና ተዳፍነው እንዲቆዩ የተደረጉላቸው ክሶች፤  እንደ አዲስ  መመዘዝ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ነው።
በተጠረጠሩበት ወንጀል ቃላቸውን እንዲሰጡ ፖሊስ ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም. በመኖርያ ቤታቸው ተገኝቶ መጥርያ ሊሰጣቸው ሲል በመሣርያ አስፈራርተው  ያመለጡት አስር አለቃ ቶሎሳ፣  ግንቦት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. በተጻፈ የክስ ቻርጅ ነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም  በሌሉበት  ክስ  ተመሰረተባቸው።

በትናንትናው ዕለት ማለትም ክሱ በተመሰረተ በሰባተኛው ወር  አቶ ቶሎሳ  በቁጥጥር ሥር ውለው በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ታስረዋል፡፡
በመምሪያው የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊውን ኢንስፔክተር ደጀኔ ከበደ  አቶ ቶሎሳ እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ  ተጠይቀው፣ ‹‹እንደማንኛውም ሰው ተይዘዋል፤ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፤ ከዚህ በላይ የምሰጠው መረጃ የለም፤›› በማለት  ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
አቶ ቶሎሳና አቶ ቦና በተጠረጠሩበት ከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ባለመቅረባቸው፣ ከአገር እንዳይወጡ እግድ መጣሉንና ፖሊስ በማንኛውም ጊዜ ይዞ ሲያቀርብ መዝገቡ መከፈት እንደሚችል በመግለጽ ለጊዜው ክሱን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስድስተኛ ወንጀል ችሎት አቋርጦት ነበር፡፡
አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በ2001 ዓመተ ምህረት የምክር ቤት አባል በነበሩበት ወቅት፤ ከአጋራቸው አቶ ቦና ታደሰ  ጋር በመሆን በ15 የግል ተበዳዮች ላይ  ወንጀል ፈጽሟል ተብለው ነው የተከሠሱት።

የክስ ቻርጁ፦ “አቶ ቶሎሳ የምክር ቤት አባል ስለሆንኩኝ ባለኝ የሕዝብ ትውውቅ መሠረት በትርፍ ጊዜዬ እየሠራሁ መሬት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አሰጣችኋለሁ፤›› በማለት፣ ከ15 ግለሰቦች ላይ በሁለት ጊዜ ክፍያ ከእያንዳንዳቸው 60 ሺሕ ብር በድምሩ 900 ሺሕ ብር ወስደዋል” ይላል ።

አቶ ቶሎሳ ተበዳዮቹን ያታለሉት፣ አቶ ቦና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በአካል በማስተዋወቅና ለእያንዳንዳቸው 200 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት እንደሚሰጧቸው ገልጸው፣ ሐሰተኛ ሰነድ (ፎርጅድ ደረሰኝ) በመስጠት መሆኑን፤ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የጠቀሰው  የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታከል።

በሌላ በኩል ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ ከተሰጠው 7 ሚሊዮን ብር አንድ ሚሊዮኑን በመቀነስ በጋራ ምክር ቤቱ ለሚሣተፉ 6 ፓርቲዎች የሰጠ ሲሆን፤ በክፍፍሉ አቶ ልደቱ አያሌው ኢዴፓ ከፍተኛውን ድርሻ አግኝቷል።

በክፍፍሉ ኢዴፓ 372ሺህ 343 ብር፣ሌሎች አምስት ፓርቲዎች ደግሞ ከ 61 ሺህ አስከ 185 ሺህ ደርሷቸዋል።

የመድረክ አባላት በጋራ ምክር ቤቱ እየተሳተፉ ያሉትን እነዚህ ፓርቲዎች፤” የኢህአዴግ  ጥላዎች፤ የኢህአዴግ  ክንፎች” ሲሏቸው ይደመጣሉ። ምርጫ ቦርክ 6 ፓርቲዎች ለሚገ በት መድረክ 3 ሺ ብር መለገሱ ይታወቃል። መድረክም ገንዘቡ ከባንክ ደብተሬ ጋር እንዳይነካካብኝ በማለት መልሶታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide