የብአዴን ባለስልጣናት ኢሳት በሚያውጣቸው መረጃዎች ዙሪያ ክርክሮችን አካሄዱ

መጋቢት ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢሳት ብአዴንን አስመልክቶ የሚያወጣቸው መረጃዎች የብአዴንን ባለስልጣናት እርስ በርስ እያወዛገባቸው ነው።በአንዳንድ አመራሮች መካከል አለመተማመኑ እየሰፋ ሂዷል።
የአማራ ክልል ጋዜጠኞች ከክልሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጋር ያደረጉት ስብሰባ የድምጽ ቅጂ ፣ በፌደራል ደረጃ በሚጠበቅ ተቋምና ከፍተኛ የኤሌክቶሪንክስ ፍተሻ በተደረገበት ሁኔታ እንዴት በኢሳት ሊወጣ ቻለ የሚል ጥያቄ ተነስቶ ባለስልጣኖቹ የተወዛገቡ ሰሆን፣ የኮሚኒኬሽን ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የአማራ ክልል ጋዜጠኞች ለተቃዋሚዎች ዱላ እያቀበሉ እያስደበደቡን ነው በማለት ጋዜጠኞችን ተጠያቂ የሚያደርግ ንግግር አድርገዋል።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ዛሬ ም/ል ጠ/ሚኒስትርና የብአዴን መሪ አቶ ደመቀ መኮንን ባሉበት በአቫንቴ ሆቴል በተደረገ ግብዣ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ መከራከራቸውም ታውቋል።
ኢሳት የክልሉን መሪ ገዱ አንዳርጋቸው ከስልጣን መነሳቱን ከዘገበ በሁዋላ፣ የብአዴን ምክር ቤት የገዱን ከስልጣን መነሳት ይፋ እናድርገው ወይስ አናድርገው በሚለው ላይ ሲወዛገብ አምሽቷል። ምክር ቤቱ እስከ ምሽቱ 2 ሰአት የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅና አወዛጋቢ ዳኞች ሹመት ላይ በመከራከር ቢያሳልፍም፣ በመጨረሻው አጀንዳ ላይ የአቶ ገዱ ጉዳይ ለምክር ቤቱ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ፣ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ስምምነት ላይ ባለመድረሱ አጀንዳው ሳይቀርብ ቀርቷል።
አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት መረጃው አስቀድሞ ከደረሳቸው በሁዋላ፣ ምሽት ላይ ምክር ቤቱን ጥለው የወጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የምክር ቤት አባላት ደግሞ ከብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የሚላክላቸውን የውሳኔ ሃሳብ እየተጠባበቁ እስከ ምሽቱ 2 ሰአት ቢቆዩም የውሳኔው ሃሳብ እንደማይደርስ ሲያውቁ ተበትነዋል። የክልል ምክር ቤቱ ስብሰባ በክልሉ ሚዲያ በቀጥታ ሲተላለፍ ከቆየ በሁዋላ፣ ከምሽተ 12 ሰአት ላይ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሆኑት መካከል ሊ/መንበሩ ደመቀ መኮንን፣ አለምነው መኮንን፣ ብናልፍ አንዷለም፣ ተስፋዬ ጌታቸው፣ አህመድ አብተው፣ ከበደ ጫኔ፣ ካሳ ተክለብርሃንና ዶ/ር አምባቸው መሰለ ፣ የኢህአዴግ ውሳኔ አሁኑኑ ተግባራዊ መሆን አለበት የሚል ሃሳብ የሰነዘሩ ሲሆን፣ በድርጅቱ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተደረጉት ነባሮቹ አቶ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ እንዲሁም ይናገር ደሴና ንጉሱ ጥላሁን ፣ የአቶ ገዱን መውረድ ይፋ ማድረግ ሊያስከትለው የሚችለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እስክንረጋጋ ብንይዘው ይሻላል፣ ወደ ባሰ እልቂት ልንገባ አይገባም የሚል አቋም አንጸባርቀዋል። አቶ በረከት “የነውጥ ሃይሎች ገዱ የፈቀደልህን የጦር መሳሪያ ሊቀሙህ ነውና ተጠቀምበት በማለት ሊቀሰቅሱብን ስለሚችሉ ፣ የገዱን መልቀቅ ይፋ ባናደርገው ይሻላል” የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸው ታውቋል።
ባለስልጣናቱ እስከ ምሽቱ 4፣30 ሰአት ድረስ መስማማት ባለመቻላቸው ስብሰባውን ለቅዳሜና እሁድ አስተላልፈውታል። በአቶ አለምነውና በአቶ ገዱ ደጋዎች መካከል ግልጽ የሚታየው ልዩነት ግልጽ የሆነ መምጣቱንም ምንጮች ገልጸዋል።
ማእከላዊ ኮሚቴው ቅድሜና እሁድ ከሚያያቸው አጀንዳዎች መካከል ኢሳት ብአዴንን በተመለከተ በሚያቀርባቸውን ዘጋባዎች ላይ ተወያይቶ እርምጃ መውሰድ የሚል ይገኝበታል። እንዲሁም ህወሃት በብአዴን ላይ ያለውን አቋም እና አሁን በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ውይይት አድርጎ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎም ይጠበቃል።
አቶ ገዱ ለድርጅታቸው ያላቸው ታማኝነት እንደተጠበቀ ቢሆንም፣ የክልሉ ህዝብ ማሳሪያ እንዲታጠቅ መፍቀዳቸውና ከትግራይ ክልል መሪ አባይ ወልዱ ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት የድንበር ውዝግቡ በጊዜው እንዲፈተና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን አድርጓል የሚል ሂስ ተሰንዝሮባቸዋል።