የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ለሁለት ተከፍለው በባህርዳር በነበረው አድማ ዙሪያ መወዛገባቸው ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 18/2009) የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ለሁለት ተከፍለው በባህርዳር በነበረው አድማ ዙሪያ መወዛገባቸው ተሰማ።

በባህርዳር ከአድማው ጋር ተያይዞ የታሰሩት ታዋቂ ነጋዴዎች ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ የተካሔደ አልነበረም በሚል የተወሰኑት የብአዴን ማእከላዊ አባላት በግልጽ በማንሳት ተከራክረዋል።

ነጋዴዎቹም ከእስር የተለቀቁት ይህ ውዝግብ በማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ከተካሄደ በኋላ በማግስቱ መሆኑ ታውቋል።
ብአዴን በሶስትና በአራት የተከፈል ቡድን እንዳለውም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ከተካሄደው አድማ ጋር ተያይዞ ታስረው በነበሩት ታዋቂ ነጋዴዎች ምክንያት የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሁለት ተከፍለው መወዛገባቸውን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የፓርቲው የቅርብ ምንጮች እንደገለጹት በብአዴን ዋና ጸሐፊ አቶ አለምነህ መኮንን የተመራው ቡድን ታዋቂ ነጋዴዎች አድማው እንዲደረግ እገዛ ሰጥተዋል በሚል መታሰራቸውን ይደግፋል።የዚህ ቡድን አባላት በባህርዳር የተካሄደው አድማ ሕገመንግስቱን ይጥሳል ባይ ናቸው።
በብአዴኑ ጽሐፊ አለምነህ መኮንን የሚመሩት እነዚሁ የሕወሀት ትዛዝ ተቀባዮች የአማራ ተወላጅ ነጋዴዎች እንዲታሰሩ ቢያደረጉም ሊሎች በከተማዋ ያሉ የትግራይ ተወላጅ ነጋዴዎች በእስር እርምጃው እንዳይካትቱ ጥንቃቄ እንዲደርግ ጥዛዝ ሰጥተዋል ተብሏል።

በሌላ ወገን ያሉትና የነጋዴዎችን መታሰር የሚቃወሙት የተወሰኑ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ግን ሕዝቡ ያካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞ በመሆኑ ሕገመንግስቱን ተከትሎ የተደረገ ነው በሚል ተከራክረዋል።

እናም ነጋዴዎችን በጅምላ ማሰር ህዝብን ከፓርቲው ይበልጥ እንዲነጠል ያደርገዋል በማለት የእነ አቶ አለምነውን የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ቡድን ተቃውመዋል።

መከራከሪያ ነጥባቸው ደግሞ በሕዝባዊ እምቢተኝነቱ የተገደሉት ከ50 በላይ ወጣቶች በሌሎች ተገፍተውም ቢሆን ምንም የማያውቁ ሕጻናትና ወጣቶች በመሆናቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ብአዴንም በሐዘን ሊያስታውሳቸው ይገባ ነበር የሚል ነው። ሕዝቡ ከቤቱ ባለመውጣት ማሰቡ ከሁከት ይልቅ ሰላማዊ ተቃውሞ መሆኑንም ያመለክታል።ይህ ደግሞ ሕገመንግስታዊ መብት ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

በመጨረሻም ነጋዴዎቹ መፈታት እንዳለባቸው የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በመስማማታቸው ከእስር እንዲለቀቁ መደረጋቸውን ነው ምንጮቻችን የገለጹት።

እነዚሁ የቅርብ ምንጮች እንደሚሉት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በ3 እና በ4 የተከፈሉ ናቸው።ይህም በአካባቢ ልጅነትና በጓደኝነት እንዲሁም ከሕወሃት ጋር ባላቸው ቅርበት እንደሚወሰን ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።ከጥቅም ጋር የተሳሰሩት የብአዴን ባለሰልጣናት ደግሞ በስራቸው ያሉ ነጋዴዎች እንዳይነኩ ለማድርግ ሲሚክሩ እርስበርስ ይጋጫሉ።

ከሕወሃት ጋር ቅርበት ያላቸውና በቀጥታ የትግራይ ተወላጅ ባለስልጣናትን ትእዛዝ ይቀበላሉ የሚባሉት በረከት ስምኦን፥ ካሳ ተክለብርሃን፣ከበደ ጫኔ፣ጌታቸው እምባዬ እና አለምነህ መኮንን ናቸው።
በክልላችን ያለውን ችግር ያለማንም ጣልቃገብነት እንፍታ የሚሉት ደግሞ ደመቀ መኮንን ፥ ዶር አምባቸው ገዱ እንዳርጋቸው፣ ብናልፍ አንዱአልም፣ንጉሱ ጥላሁንና ሙሉጌታ ወርቁ እንዲሁም የጎንደርና የጎጃም ተወላጅ የሆኑ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

አለምነህ መኮንን ከአዲስ አበባው በረከት ስምኦንና ከነጌታቸው አምባዬ ትእዛዝ እየተቀበለ ጌታቸው ጀምበርን፣ፍስሃ ወልደሰንበትንና ሌሎችንም ይዞ የሕወሃትን አጀንዳ በአማራ ክልል ለማስፈጸም የሚሯሯጥ ሰው መሆኑ ይነገራል።

አለምነህ መኮንን የአማራን ሕዝብ በማሰደብ በሕብረተሰቡ መጠላቱን ስለሚያውቅ ከሕወሃት ጋር የሚመጡ ትእዛዞችን ያልምንም ማወላዳት ለማስፈጸም ዝግጁ ነው ተብሏል።
በአቶ ደመቀ መኮንንና በክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል ያሉት ደግሞ የአማራን ጉዳይ ለእኛው ተውት የሚሉና ችግሩን እራሳችን እንፈታለን ባይ ናቸው።

የወልቃይትን ጉዳይ የቅማንትንና የግጨውን የህዝብ አጀንዳዎች በውይይት እንፈታዋለን በሚል በራሳቸው መንገድ መራመድ የሚፈልጉ መሆናቸው ተነግሯል።
በ3ኛ ረድፍ የተሰለፉት ደግሞ አኩራፊዎችና መሀል ሰፋሪዎች የተባሉ የብአዴን ከፍተኛ ካድሬዎች ይገኙበታል።

እነዚህም ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት የተገለሉና ከነበሩበት ከፍተኛ ስልጣን ገሸሽ የተደረጉ ናቸው።እነዚህም ብርሃን ሃይሉ፣ተፈራ ደርበው፣ብስራት ጠናጋሻው፣ተሰማ ገብረህይወትና መሰል ቅሬታ ያለባቸው ናቸው ተብሏል።

በ4ኛ ረድፍ ያሉትና የሽምግልና እና የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉት ደግሞ አዲሱ ለገሰ፣ተፈራ ዋልዋ፣ሕላዊ ዮሴፍ፣ታደሰ ካሳ፣ዮሴፍ ረታና በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበረው ውለታው የሚባል ሰውን ጨምሮ የቀድሞው የብአዴን ከፍተኛ አመራር አባላት ናቸው።

ያም ተባለ ያሕ ግን የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በየትኛውም ረድፍ ቢሰለፉና የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖራቸው ሁሉም የሕዝብ ጠላት ናቸው የሚሉ በርካቶች ናቸው።