የብሪታኒያ መንግስት ለአለም አቀፍ ዕርዳታ ድጋፍ ለማስቀረት አዲስ እቅድ መንደፉ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2009)

የብሪታኒያ መንግስት በየአመቱ ለአለም አቀፍ ዕርዳታ የሚሰጠውን 12 ቢሊዮን ፖውንድ ድጋፍ ለማስቀረት አዲስ እቅድ መንደፉ ተገለጸ።

የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ፓርቲያቸው በቀጣዩ ወር በሚካሄደው የምርጫ ሂደት ሃሳቡን ያሳውቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሪታኒያው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ደሃ ሃገራት ብሪታኒያ ለአለም አቀፍ እርዳታ ከምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነው መቆየታቸው ታውቋል።

ይሁንና ብሪታኒያ ለተለያዩ ሃገራት የምትሰጠው ድጋፍ የታለመለትን ግብ አልመታም በሚል የሃገሪቱ ፖለቲከኞች በገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥያቄን እያነሱ እንደሚገኝ ጋዜጣው በሪፖርቱ አቅርቧል።

የብሪታኒያ መንግስት ከጥቂት አመታት በፊት በገባው ቃል መሰረት ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ወይም ገቢ 0.7 በመቶ የሚሆነውን ለአለም አቀፍ ዕርዳታ ለማዋል መወሰኑ ይታወሳል።

የዚህኑ ውሳኔ ተከትሎ ሃገሪቱ በየአመቱ 12 ቢሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ ለዚሁ አላማ ስታውል ቆይታለች።

ይሁንና፣ በሃገሪቱ በቅርቡ ለስልጣን የበቃው አዲስ ፓርቲ አለም አቀፍ ድጋፍ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን ለመውሰድ እቅድ እንዳለው አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሜይ ዝርዝር መረጃውን በምርጫ ዘመቻው ወቅት የሚታወቅ ይሆናል ሲሉ መረጃን ከመስጠት እንደተቆጠቡ ቢቢስ አመልክቷል።

አለም አቀፍ ዕርዳታ ለደሃ ሃገራት ጠቅሜታ አለው የሚል ሃሳብን የሚያራምዱት ባለሃብቱ ቢል ጌትስ ብሪታኒያ ስትሰጥ የቆየቸውን ድጋፍ እንዳታቋርጥ ጥያቄን አቅርበዋል።

የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ ብሪታኒያ የምትወስደው ዕርምጃ በደሃ ሃገራት የሚካሄዱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎችን በማዳከም ለሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሃገሪቱ ለደሃ ሃገራት ስትሰጥ የቆየችው በሽታዎችን ስርጭት ለመቆጣጠርና እንዲሁም የስደተኞች ፍልሰትን ለመቀነስ አስተዋጽዖ ማድረጉን ቢሊየነሩ ባለሃብት አክለው ገልጸዋል። ወግ አጥባቂ እንደሆነ የሚነገርለት የብሪታኒያው አዲሱ መንግስት በገንዘብ አጠቃቀም ላይ ጠንካራ አቋምን ለመከተል ግፊት እንደበረታበት ለመረዳት ተችሏል።

ፓርቲው በቅርቡ ሊወስዱ በታቀዱ የአለም አቀፍ ድጋፎች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያን ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የፓርላማ አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለባቸው ለሚባሉ ሃገራት ድጋፍ እንዳታደርግ ዘመቻ መክፈታቸውም ታውቋል።

ከወራት በፊት ሃገሪቱ በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የማህበረሰባዊ የመገናኛ ብዙሃን ትምህርቶች ልትሰጥ የነበረው አምስት ሚሊዮን ፓውንድ (ከ 150 ሚሊዮን ብር በላይ) በተመሳሳይ ዘመቻ እንዲቀር መደረጉ ይታወሳል።

የፓርላማ አባላቱ ለዘርፉ ሲሰጥ የቆየው ድጋፍ ያመጣው ለውጥ የለም በማለት የገንዘብ ልገሳው እንዲቋረጥ ሰፊ ዘመቻ ማካሄዳቸውን ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።

ባለሃብቱ ቢል ጌትስ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በተመሳሳይ መልኩ ለአለም አቀፍ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ ሊወሰድ ያቀደው የማስተካከያ ዕርምጃ ተግባራዊ እንዳይሆን ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን ከብሪታኒያ መንግስት ጋር በመተባበር ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት ወባን ጨምሮ የተላላፊ በሽታ ስርጭቶችን ለመከላከል በጋራ እየሰራ መሆኑም ታውቋል።