የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት በሶማሊያ የሚገኙ የሃገሪቱ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከሃገሪቱ መውጣት እንዲጀምሩ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 8፥ 2009)

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት በሶማሊያ የሚገኙ የሃገሪቱ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከሃገሪቱ መውጣት እንዲጀምሩ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገለጸ።

የቡሩንዲ ባለስልጣናት ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሊያ ተሰማርተው የሚገኙ ከ5ሺ በላይ ሰላም አስከባሪዎች ደሞዛቸው ባለመከፈሉ ምክንያት ከሶማሊያ ጠቅልልለው እንደሚወጡ ሲያሳስቡ መሰንበታቸው ይታወሳል።

የማላዊ መንግስት ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ሲያካሄዱ የቆዩቱን ውይይት ተከትሎ 5ሺ 400 የሚሆኑ የሃገሪቱ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከሶማሊያ መውጣት እንዲጀምሩ ሰኞ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ጋስቶን ሲንዶሞ’ኣ የተባሉ የቡሩንዲ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን በቅርቡ ወታደሮቹ እንዲወጡ የቀረበው ሃሳብ ውሳኔ ማግኘቱና ወታደሮቹ ከሶማሊያ መውጣት እንዲጀምሩ ለዜና አውታሩ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይልን በገንዘብ ሲረዳ የነበረው የአውሮፓ ህብረት ለልዑኩ ሲሰጥ የነበረው ድጋፍ እንዲቀንስ በማድረጉ ምክንያት የሰላም አስከባሪ ሃይልን ያዋጡ የአፍሪካ ሃገራት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ብሩንዲ በሶማሊያ ያሰማራቻቸውን ወታደሮች ለማስወጣት ቀዳሚ ሃገር የሆነች ሲሆን፣ ማላዊ እና ዩጋንዳም ወታደሮቻቸውን ከሃገሪቱ ለማስወጣት ፍላጎት እንዳላቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ የሚሰጠውን ድጋፍ መቀነሱ በሰላም ማስከበር ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል ሲል ስጋቱን ይገልጻል።

የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ላለፉት 10 አመታት በሶማሊያ ከፍተኛ ገንዘብ በመደደብ የሰላም አከባሪ ሃይል ለማሰማራት የተደረገው ጥረት በሃገሪቱ የሚፈለገውን ሰላምና መረጋጋት ማምጣት እንዳልቻለ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ ኬንያ፣ና ጅቡቲ የተውጣቱ ወደ 22ሺ አካባቢ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም በሃገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር መሻሻል አለማሳየቱም ይነገራል።

አልሸባብ የተሰኘ ታጣቂ ሃይል በመዲናይቱ ሞቃዲሾ እና የተለያዩ ግዛቶች እያደረሰ ያለው ጥቃትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሶማሊያ ባለስልጣናት እና መገናኛ ብዙሃን ይገልጻሉ።