የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

ኢሳት (ኅዳር 30 ፥ 2009)

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። በደርግ ኢህድሪ መንግስት ውስጥ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉትና በመጨረሻ ለከፍተኛው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስፍራ የበቁት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ያረፉት በስደት በሚገኙበት በዩ ኤስ አሜሪካ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የህይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው የዛሬ 77 አመት በምዕራብ ኢትዮጵያ አምቦ አቅራቢያ የተወለዱት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ጀኔራል ዊንጌት ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሊባኖስን ቤይሩት የአሜሪካ ዩኒቨስርቲ አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዩ ኤስ አሜሪካ ኒው ዮርክ በሚገኘው ሲራኪዩዝ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደርና በኢንጂኔሪንግ ሁለት ዲግሪዎችን ተቀብለዋል።

ግንቦት 19 ቀን 1983 በደርግ ኢህድሪ መንግስት፣ በሻዕቢያ፣ ኢህአዴግና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መካከል ሊካሄድ በታቀደው ድርድር የመንግስት ልዑካን መርተው ለንደን የተገኙት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ፣ የድርድሩን ሂደት በመቃወም በወቅቱ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

በዚያም የስደትን ህይወት የጀመሩትና ላለፉት 25 አመታት በዩ ኤስ አሜሪካ የቆዩት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ፣ በአለም ባንክና መሰል አለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ሲያገለግሉ መቆየታቸውን መረዳት ተችሏል።

በስደት በሚገኙበት ዩ ኤስ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ቨርጂኒያ ግዛት ቬይና ውስጥ ህይወታቸው ያለፈው የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የቀበር ስነስርዓት ቅዳሜ ታህሳስ 1 ፥ 2009 (December 10 2016) በዚሁ በአሜሪካ እንደሚፈጸም መረዳት ተችሏል።

አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ኢትዮጵያ በደርግ አመታት “Ethiopia during the Derg Years” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሃፍ ህትመቱ በተጠናቀቀበት ወቅት ማለፋቸውንም መረዳት ተችሏል።

መጽሃፉን ካሳተመው ጸሃይ ፐብሊሸር ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ወንድሙ መረዳት እንደተቻለው ይኸው የአቶ ተስፋዬ ዲንቃ መጽሃፍ በቀጣይ ወር ለህዝብ ይሰራጫል።

አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ““Ethiopia during the Derg Years” በሚለው መጽሃፋቸው የደርግ የስልጣል ዘመን እስከ ፍጻሜው የሚዳስስ፣ የለንደኑን ኮንፈረንስ ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን በሚዘረዝር ባለ 330 ገፅ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

አቶ አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የ 4 ልጆች አባትና የ4 ልጆች አያት ነበሩ።