የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ግንቦት ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በልዩ የእግር ኳስ ክህሎቱ በመላው ኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ አድናቂዎች ተወዳጁ አሰግድ ተስፋዬ ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በድንገት መታጠቢያ ቤት ውስጥ በመውደቁ ሕይወቱ አልፏል። አሰግድ ተስፋዬ በ1962 ዓ.ም በድሬደዋ ከተማ ደቻቱ ውስጥ ተወልዶ በ47 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ዓመለ ሸጋው አሰግድ ተስፋዬ ለድሬደዋ ጨርቃጨርቅ፣ መድህን ድርጅት፣ ቅዱስጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ቡድኖች ተዟዙሮ ተጫውቷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከወጣት እስከ ዋናው ብሄራዊ ቡድን በአጥቂነት ተሰልፎ አገሩን አገልግሏል።
በተለይ በኢትዮጵያ ቡና በነበረው ቆይታ ያሳለፋቸው ጊዜያት ታላቁን የስኬት ዘመን አሳልፍዋል። አሰግድ ተስፋዬ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት መሆኑም በግለ ታሪኩ ላይ ሰፍሯል።
ለመላው ቤተሰቦቹ አድናቂዎቹ እና እግር ኳስ ወዳዶች መጽናናትን ይስጣቸው።