የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ነቢቡ በ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው በፍትህ እጦት እየተሰቃዩ ነው

ግንቦት ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንጮች እንደገለጹት የ3 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ነቢቡ ደሳለኝ ላለፉት 3 ወራት በ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስረው እየተሰቃዩ ሲሆን፣ ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም መልስ አለማግኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ወ/ሮ ነቢቡ በአሸባሪነት እንደምትከሰስ የተነገራቸው ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግን ምንም የክስ ቻርጅ አልቀረበባቸውም። በመሃሉ በፍትህ እጦት እርሳቸውና ልጆቻቸው ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጋቸውን የወ/ሮ ነቢቡ የቅርብ ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ከወ/ሮ ነቢቡ ጋር አቶ አዝመራው የሚባል ግለሰብም እንዲሁ ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ በእርሳቸው ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። ግለሰቡ በከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ ቢሆንም፣ እስካሁን ህክምና አለማግኘታቸውም ታውቋል።
ወ/ሮ ነቢቡ ለ3ኛ ጊዜ በመጪው ግንቦት 19፣ 2009 ዓም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።