የሶማሊ ልዩ ሃይል ታጣቂዎች በኦሮምያ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ፈጸሙ

የካቲት ፫ ( ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ የኢሳት ወኪል እንደዘገበው ከፍተኛ የህወሃት ድጋፍ ባላቸው በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ የሚመራው ልዩ ሃይል በኦሮሞያ ክልል ከባቢሌ በ18 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በሚገኙት በአውሸሪፍና ደረሬ ቀበሌዎች በመግባት ከኦሮምያ ፖሊስ ጋር የተዋጋ ሲሆን ፣ በውጊያውም አንድ የኦሮምያ ፖሊስ ሲገደል ፣ ሁለት ፖሊሶች ተማርከው ተወስደዋል። ይሁን እንጅ በሁሉቱ ሃይሎች መካከል በተደረገ ድርድር የተያዙት ፖሊሶች ዛሬ እንዲመለሱ ተደርጓል።
በጉሩሱም አካባቢም እንዲሁ የሶማሊ ልዩ ሃይል የገባ ሲሆን፣ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ተከስቷል። የሁለቱ ክልል መንግስታትና የፌደራሉ መንግስት ባደረጉት ውይይት፣ በአወዛጋቢዎቹ የድንበር ከተሞች የመከላከያ ሰራዊት እንዲገባ፣ የሁለቱም ክልሎች ታጣቂዎች ከአካባቢው እንዲርቁ ተወስኖ ነበር። በዚህ ውሳኔ መሰረት መካለከያ ሰራዊት በአካባቢው ቢሰፍርም፣ በሶማሊ ልዩ ሃይል ሚሊሺያዎች ላይ ምንም እርምጃ አልወሰደም።
በሌላ በኩል የምስራቅ እዝ ሃላፊዎች በአካባቢው በተለይም በኦሮምያ ክልል የድንበር ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች የጦር መሳሪያዎችን እንዴት ሊያገኙ ቻሉ የሚል ምርመራ መጀመራቸው ታውቋል። በጉሩስምና ቦምባሳ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለቀናት የሚደርስባቸውን ጥቃት መቋቋም መቻላቸው በምስራቅ እዝ አዛዦች ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል። የአካባቢውን ነዋሪዎች የኦሮምያ ፖሊስ እያስታጠቃቸው ነው የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም፣ ጉዳዩ ከሶማሊ ላንድ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል በመገመት የሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንትና የመከላከያ ሚኒስትሩን ጨምሮ 6 ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ስብሰባ በማድረግ ላይ ናቸው።
ለስብሰባው መንስኤ ምክንያት ከሆኑት መካከል በሶማሊላንድ በእስር ላይ የነበሩ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆችን ያለ ህወሃት/ኢህአዴግ እውቅና መፈታታቸው ሲሆን፣ በሶማሊ ላንድ በኩል የጦር መሳሪያ ወደ አካባቢው እየገባ ነው የሚለውም ሌላ ምክንያት መሆኑን የኢሳት የደህንነት ምንጮች ይገልጻሉ።
በተለይም ሶማሊላንድ ወደቧን ለዱባይ ማከራየቷ ፣ ለግብጽ ለእንስሳት ማድለቢያ በሚል መሬት መስጠቷ፣ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ የደህንነት አባላት ጋር የመረጃ ለውውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ፣ የጦር መሳሪያ ወደ አካባቢው እየገባ ነው ከሚለው ግምት ጋር ተያይዞ በአካባቢው ያለው የደህንነት ሁኔታ ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን ምንጮች ይገልጻሉ።
የኦሮምያ ክልል አንዳንድ ባለስልጣናት ግን ህወሃት በሶማሊ ልዩ ሃይል አማካኝነት ሆን ብሎ በኦሮምያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር የሚጠቀምበት ዘዴ ነው በማለት ወቀሳ ያቀርባሉ።