የሶማሊንና የኦሮሚያን የክልል መንግስታት እያወዛገበ ያለው የሞያሌን ከተማ እና አካባቢውን አስተዳደር በፌደራል መንግስቱ ስር ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ጥር 20 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሶማሊንና የኦሮሚያን የክልል መንግስታት እያወዛገበ ያለውና በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በርካታ ዜጎች ለሞትና ለስደት የሚዳረጉበትን የሞያሌን ከተማ እና አካባቢውን አስተዳደር በፌደራል መንግስቱ ስር ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀመረ::

የኢሳት የሞያሌ ምንጮች እንደገለጡት ከወራት በፊት በሶማሊና በኦሮሚያ ብሄሮች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በከተማዋ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ተሰማርቷል።

በአሁኑ ጊዜም በቦረና እና በገሪ ጎሳዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ነው።

የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት አካባቢውን ለማስተዳደር ባለመቻላቸው የፌደራሉ መንግስት ሞያሌን በራሱ ግዛት ስር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

ሞያሌ በሁለት ክልል መንግስታት ትተዳደራለች። በከተማዋ ውስጥ የሶማሊ እና የኦሮምያ ክልል መስሪያቤቶች ይገኛሉ።   ከኦሮሞ እና ሶማሊ ክልሎች ያልተወለዱ ነዋሪዎች ችግሮች ሲገጥሙዋቸው ለየትኛው መስሪያ ቤት ማመልከት እንዳለባቸው አያውቁም።