የሱዳን የጦር መኮንኖች ለፕሬዝዳንት አልበሽርና ለመከላከያ ሚኒስትራቸዉ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

ጥር 22 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ደቡብ ሱዳንን ለመዉጋት ከሚያደርጉት ችኮላ እንዲቆጠቡና ሌሎችም ወታደራዊና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ ለአልበሽርና ለመከላከያ ሚነስትራቸዉ ፣ ለአብዱል ረህማን መሃመድ ሁሴን ማስጠንቀቂያዉን የሰጡት ፣ ቁጥራቸዉ 700 የሚሆኑ የሱዳን የጦር ሃይል መኮንኖች እንደሆኑ ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ ዘግቧል።

ከደቡብ ሱዳን ጋር ባለ ችግር ምክንያት ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ፕሬዝዳንቱና የመከላከያ ሚኒስትሩ ለጦር መኮንኖቹ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ፣ መኮንኖቹ  በጦሩ ዉስጥ ያሉትን ችግሮች እስካላስወገዱ ድረስ ጦሩ በብሉ ናይል እና በደቡብ ኮርዶፋን ከሚገኙት አማፅያን ጋር ተዋግቶ ወሳኝ ድል ለመቀዳጀት እንደማይችል አስረድተዋል።

የዉጭ ጣልቃ ገብነት ሊኖር ይችላል የሚል ግምት በበዛበት በዚህን ወቅት ጦሩ የሚገጥመዉን አደጋ መቋቋም ይችል ዘንድ ብዙ ጥረት መደረግ እንዳለበት ለአልበሽርና ለሚኒስትሩ በስብሰባዉ ወቅት ተነግሯቸዋል።

እኤአ በ2010 አገሪቱ የገዛቻቸዉ 200 የሚሆኑ የዉጊያ ታንኮች ብዙዎቹ ጉድለት እንዳላቸዉና ጥቂቶቹ በጎረቤት አገር ጥገና እንደተደረገላቸዉ በምሳሌ በመግለፅ በጦሩ ዉስጥ ስር የሰደደዉ ሙስና እንዲጣራ ጠይቀዋል።

በርካታ ከፍተኛ መኮንኖች ግዢዉ ሙስና እንዳለበት በመግለፃቸዉ ምክንያት የአልበሽር ዋና ፀሃፊ የነበሩትን ጨምሮ 3 ሜጄር ጀኔራሎች ከስልጣናቸዉ መወገዳቸዉ ይታወቃል።

የጦር መኮንኖቹ ከዚህም በላይ በጦሩና በገዢዉ ብሄራዊ ኮንግሬስ ፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባዉ ልዩነት በግልፅ እንዲቀመጥና  ፓርቲዉ የሚፈፅማቸዉ ሰህተቶች በጦሩ ትከሻ ላይ እንዳይወድቁ ጦሩ ከአገሪቱ ፖለቲካ ገለልተኛ እንዲሆን ፕሬዝዳንቱንና የመከላከያ ሚኒስትሩን አሳስበዋል።

ይህን በተመለከተ መንግስታዊ መዋቅር ማሻሻያ እስካልተደረገ ድረስ የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በእስላም አክራሪዎችና በብሄራዊ ኮንግሬስ ፓርቲዉ መካከል የሚታየዉ ፍጥጫ በጦሩ ዉስጥ መስፋፋት መጀመሩ እንደምክንያት ቢቆጠርም በማስረጃ አለመረጋገጡ ተገልጿል። የጥያቄዉ መነሳትና የጦር መኮንኖቹ ማስጠንቀቂያ  ፕሬዝዳንት አልበሽርንና የመከላከያ ሚኒስተርሩን ክፉኛ እንዳስደነገጣቸዉ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።