የሰበታ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ በ10 አመት እና በ40 ሺ ብር ተቀጡ

የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከሙስና ጋር በተያያዘ በእስር ላይ በሚገኙት በርካታ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ መስጠቱን ዘጋቢአችን ገልጧል።

ከአቶ አባዱላ ገመደ እና ከወ/ሮ  አዜብ መስፍን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሲነገርላቸው በቆዩት በከንቲባ ሽመልስ ላይ የ10 አመት ፍርድ ሲያስተላልፍ፣ ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው ግበረ አበሮች ላይ ደግሞ ከ8 አመት እስከ 9 ወር በሚደርስ እስር እንዲቀጡ ወስኗል ።

በአቶ ሽመልስ ላይ ተደጋጋሚ የህዝብ አቤቱታ ሲቀርብ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ግለሰቡ በሰበታ አካባቢ ለታየው የመሬት ዝረፊያ ዋነኛ አስተባባሪ በመሆን ስማቸው በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ነበር። ከአባዱላ እና ከወ/ሮ አዜብ ጋር ባላቸው ግንኙነትም እስከ ዛሬ ሳይነኩ ቀርተዋል የሚሉ አስቴአየቶች  ይቀርቡ ነበር። ይሁን እንጅ አባዱላ ገመዳ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትነታቸው ሲነሱ፣ ከእርሳቸው ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ናቸው የተባሉት ሁሉ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ትእዛዝ እየታደኑ መታሰራቸው ይታወቃል።

አቶ አለማየሁ የወሰዱት እርምጃ አላስደሰታቸው አባዱላ ወገኖች ፕሬዚዳንቱን በመርዝ ለመግደል ሞክረው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል። አቶ አለማየሁ ስልጣናቸውን በተረከቡ በጥቂት ወራት በደረሰባቸው መመረዝ እስከ ዛሬ በህመም እንደሚሰቃዩ ይታወቃል።