የምርጫ ቦርድ፤ የአዋጁን መመዘኛ አሟልተው በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ ናቸው አለ

ጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፤ የአዋጁን መመዘኛ አሟልተው በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ  ያሉ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ ናቸው። እነሱም ኢህአዴግና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ብቻ ናቸው” ሲል ሌሎቹን ፓርቲዎች አስጠነቀቀ።

የኢህአዴግ ታማኝ ተቃዋሚዎችን ብቻ ያካተተ የውይይት የክርክር መድረክ መዘጋጀቱ፤ተቃውሞ አስነሳ።

“በምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ፣ የማደራጀት፣ የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመደገፍ ኃላፊነት አለኝ”ያለው ምርጫ ቦርድ፤ ብዙዎቹ ፕርቲዎች የአዋጁን መመዘኛ አሟልተው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም “ ሲል ጠቁሟል።
የቦርዱ የሕዝቡ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወ/ሮ የሺ ፈቃደ፤ እስካሁን በፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ መመዘኛ አሟልተው እየሰሩ ያሉት ኢህአዴግና ኢራፓ ብቻ መሆናቸውን  በመጥቀስ፤ቦርዱም ሁለቱን ፓርቲዎች ለማበረታታት ሲል የምስጋና ደብዳቤ ጽፎላቸዋል ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ማሟላት አለባቸው ያሏቸውን ስምንት መመዘኛዎች የዘረዘሩ ሲሆን፤ ከነዚህም ስምንት ነጥቦች መካከል አንዱ “ከ2002 ጠቅላላ ምርጫ እራሳቸውን ያገለሉ ፓርቲዎች ከመንግስት የተሰጣቸውን ድጋፍ መመለስ አለባቸው” የሚል ነው። በመሆኑም  በምርጫው ያልተሳተፉ ፓርቲዎች የወሰዱትን የሕዝብ ገንዘብ ሊመልሱ ይገባል ብለዋል-ሀላፊዋ።

በምርጫው የተሳተፉት አብዛኞቹ ፓርቲዎችም ሌሎች መመዘኛዎችን እንዳላሟሉ የጠቀሱት ወይዘሮ የሺ፤ አንድነት መድረክ፣ኢዴፓ፣መኢአድ፣አረና እና  ሌሎችም ፓርቲዎች በቦርዱ የተጠየቁትን እንዲያሟሉ አሣስበዋል።

አንዳንድ ፓርቲዎች ለምርጫ 2000 አነስተኛ ገንዘብ ከወሰዱ በሁዋላ በምርጫው ባለመሳተፋቸው ገንዘቡን እንዲመልሱ ምርጫ ቦርድ መጠየቁ አግባብ ነው። አስገራሚው ነገር ፤ይህችን አነስተኛ ገንዘብ ለማስመለስ ሽንጡን ገትሮ እየተከራከረ ያለው ምርጫ ቦርድ፤ ኢህአዴግ ከምርጫ አዋጁ ውጪ በሚሊዮን የሚቆጠር የመንግስትን ገንዘብና ንብረት ለምርጫ ስለማዋሉ፤በመርህ ደረጃ እንኳ ምንም ሊል አለመድፈሩ ነው ይላሉ-አስተያዬት ሰጭዎች።

“…ይባስ የሚያስቀው ደግሞ..”  ይላሉ አስተያየታቸውን ሲቋጩ ፦”ይባስ የሚያስቀው ደግሞ፤በጠራራ ጸሀይ ኮሮጆ ከመገልበጥ ጀምሮ ከምርጫ ጋር በተያያዘ በርካታ ወንጀሎችን በመፈጸም የሚታወቀው ኢህአዴግ፤ “የምርጫ መመዘኛን ያሟላ” ተብሎ በቦርዱ መጠቀሱ ነው ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ በብዙሀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ፦”ምራጭ ቦርድ” በመባል ይታወቃል።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ፤ኢህአዴግ ራሱ ከመረጣቸው ታማኝ ተቃዋሚዎቹ ጋር ቀጣዩን ምርጫ አስመልክቶ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፍ የክርክር መድረክ ማዘጋጀቱ ተሰማ።

ይህ አንጋፋዎቹን ፓርቲዎች በማግለል ሊዘጋጅ የታሰበው የክርክር መድረክ፤በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ክርክሩ የሚካሄደውም  በአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ፦ ህወሀት፣ብአዴን፣ኦህአዴድና ደኢህአዴግ፤እንዲሁም  የአፋር ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ፤ (አብዴፓ)፣ የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ሶህዴፓ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ጋህዴፓ)፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ(ቤጉሕዴፓ) ፣  የሀረሪ ብሔራዊ ሊግ ንቅናቄ(ሐብሊን)በተሰኙት የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች እና በኢዴፓ፣ በአቶ አየለ ጫሚሶ በሚመራው ቅንጅት፣ኢፍዴአግ እና አብዴፓ መካከል ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦህዴፓ) ፤ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ክርክር ሊጀምሩ ነው መባሉን ተከትሎ፦ “ ክርክሩ በኢህአዴግ ቀኝ እና ግራ ክንፍ መካከል የሚደረግ ክርክር ነው “በማለት ነው የተቃወመው።

የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ፦” ኢህአዴግ  የሁለቱን ልጆቹን ክርክር፤ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ክርክር አስመስሎ ለማቅረብ የሚያደርገው ሙከራ  ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ፤ መገናኛ ብዙሀኑም  “ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ክርክር ይደረጋል እያሉ የሚነዙትን ፕሮፓጋንዳ እንዲያቆሙ ጠይቋል።