የሜድሮክ ኩባንያ ለገደንቢ ላይ ሲያካሄድ የነበረው ወርቅ የማውጣት ፈቃድ እንዲታደስለት ፈቃድ ጠየቀ

ሰኔ 21 ፥ 2009

የሼህ መሐመድ አላሙዲ ንብረት የሆነው ሜድሮክ የወርቅ ማውጫ ኩባንያ በኦሮሚያ ለገደንቢ ላይ ለ20 አመታት ሲያካሂድ የነበረው የወርቅ ማውጣት ስራውን ለመቀጠል የሚያስችለው ፈቃድ አንዲታደስለት ጠየቀ።

ኩባንያው ስምምነቱ ሊጠናቀቅ አንድ አመት ስለቀረው በለገደንቢ በብቸኝነት ሲያካሄደው የነበረውን የወርቅ ማውጣት ስራ ለማስቀጠል ለማዕድን የነዳጅና የተፈጥሮ ሐብት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል።

ጥያቄው የቀረበላቸው ሚኒስቴር አቶ ሞቱማ መካሳ ጉዳዩን እያጤኑት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በተለይም ጉዳዩን እየመረመሩ ያሉት የመአድን ፈቃድና አስተዳደር ስራውን የሚመለከታቸው ሚኒስተር ዴኤታው አቶ ቴዎድሮስ ገብረእግዚያብሄር በመሆናቸው የእርሳቸው ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል ።

የሼህ መሀመድ አላሙዲንና በባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ሳሊህ ንብረት ስም ያለው ሜድሮክ ወርቅ ከ1990 ጀምሮ የወርቅ ማውጣት ስራው ከመንግስት ተረክቦ ላለፉት 20 አመታት ሲጠቀምበት ቆይቷል። መንግስት የወርቅ መአድን ስራውን በወቅቱ 2 በመቶ የራሱን ድርሻ በመያዝ ለሼህ መሀመድ በ 172 ሚሊዮን ዶላር መሸጡም ይነገራል።

ሜድሮክ ንብረቱን ከተረከብ በኋላ በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ብቻ 34,000 ኪሎ ግራም ወርቅ በማውጣት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ዘገባው አመልክቷል ።

በኦሮሚያ ክልል ለገደምቢ ባሉ ስፍራዎች የወርቅ ማውጣት ስራውን እያስፋፋው ያለው ሜድሮክ የውል ስምምነቱ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ ለሌላ ዙር ቀጣዩ ስራው ውሉ አንዲታደስለት ጠይቋል ። ሜድሮክ በተመሳሳይ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ማውጣት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ይታወቃል። ከዚህ ስራው 27 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ ከወርቅ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የውጪ ምንዛሬ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በቅርብ ለፓርላማ ሪፖርቱን ያቀረበው የነዳጅ የተፈጥሮ ሃብትና የማዕድን ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።