የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያለበትን ቦታ አናውቅም አሉ

ታኅሣሥ  ፭ (አምስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ህብረት መንግስት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያለበትን ቦታ እንዲያሳውቅ መጠየቁን የዘገበው አሶሺየትድ ፕሬስ፣ የኢትዮጰያ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር  የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ግዛቸው መንግስቴ  ጋዜጠኛ ተመስገን ያለበትን ቦታ እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 2014 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ህብረቱ  ዛሬ እንዳለው  ከሁለት ኣመት እስር በሁዋላ ጋዜጠኛውን   መሰወርና ስላለበት ሁኔታ ለቤተሰቦቹ ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው።

ጋዜጠኛ ተመስገን አሳማኝ ባልሆነ ክስ መታሰሩን የጠቀሰው የሰብአዊ መብት ቡድኑ፤ በስም ማጥፋትና አመጽ በማነሳሳት የተፈረደበትን የሶስት ዓመት እስራት እየተቀበለ መቆየቱን አውስቷል።